ገ ረ ገ ራ     በማንኛዉም የመጽሐፍ አዟሪና መደብር ይገኛል።     Order4Delivery (እዚሁ ያዝዙ)
ግለ ታሪክ

የከባለ ተሞክሮ አንጋፋዎችና ወጣቶች ግለ ታሪክ

፩) ትውልድ(ቀንና ቦታ)፣ ቤተሠብ፣ ትምህርት

አባቱ አለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ማርያም ይባላል፡፡ አለቃ ለማ የኢትዮጵያን የቀድሞ ሊቅነት ያሟሉ ተጠቃሽ ሊቅ ነበሩ፡፡ በስም አጠራራቸውም የእናታቸውን ስም መያዙ(ታሪክ የእናታቸው ስም ነዉና) የመጀመሪያ ያስባላቸው አስተዋይ ሰው ነበሩ፡፡ የእናታቸው ስም ደግሞ ወይዘሮ አልማዝ ይልማ ይባላል፡፡ እናም ደማሙ ብዕረኛ መንግስቱ ለማ ሰኔ 1 ቀን 1916 ዓ.ም ሐረር አደሬ ጢቆ በተባለ አካባቢ ተወለደ።

አባቱ፣ ታዋቂ የቤተክርስቲያን ሊቅ የነበሩ ሲሆን በመጀመሪያ ላይ የመንግስቱን የአስኳላ ትምህርት ባይወዱለትም ጣሊያኖቹ ልጁን የማያስተምር ሰው ሁሉ ይቀጡ ስለነበር ለማስተማር ተገደዋል። ቆይቶ ግን እሳቸው አዲስ አበባ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ ተቀይረው መጥተው እሱ የኮተቤ ተማሪ ከሆነና የትምህርት ውጤቱም አስደሳች ሲሆን የቀድሞ አቋማቸውን ሳያላሉት አልቀሩም። ስለሆነም፤ በጣሊያን ወረራ ዋዜማ በሀረር ሀደሬ ጢቆ መካነ ሥላሴ ተወልዶ ከቆሎ ተማሪነት ተነስቶ የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ደቀመዝሙርነት እስከመሆን በቅቶ የቅኔ ቤት ሊቅነት ሳይበቃው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ቀደምቶች መሃከል ለመቆጠር የበቃ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ድንቅ ገጣምያን/ፀሃፌ ተውኔቶች አንዱ ነው- መንግስቱ ለማ።

ትዳሩን በተመለከተም ያየን እንደሆነ ከየሺ ወ/ቂርቆስ ጋር ተጋብቶ የውብ ድንበር መንግስቱንና አለማየሁ መንግስቱን ወልዷል፡፡

፪) ሙያ፣ አስተዋጽዖ፣ ተሰጥዖ

ከጋሽ መንግስቱ ዕልፍ ግጥሞች መካከል ቀጣዩ ባብዛኛው የግጥም ወዳጅ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይኸው፡-

በጠራ ጨረቃ በእኩለ ሌሊት

ዓይኖቿ እየበሩ እንደ ከዋክብት

“ሳማት! ሳማት “አሉት

“እቀፍ! እቀፋት!”

አላወላወለም ወጣቱ ታዘዘ

ወገቧን አንገቷን እጇን በጁ ያዘ።

ምንም እንኳ ጡቷ እንደሾህ ቢዋጋ

ጣቷ በመሆኑ የጉማሬ አለንጋ

ጆሮ ግንዱን ስማው በጥፊ ሲናጋ።

ዋ ጀማሪ መሆን! ዋ ተማሪነት

ዋ ትዕዛዝ መፈጸም ዋ ምክር መስማት

በጠራ ጨረቃ በኩለ ሌሊት።

መንግስቱ ባባቱ አካሄድ ሃገራዊውን የቤተ ክርስትያን ትምህርት በጠና ተምሮ ሲያበቃ፣ በእንግሊዝ አገር ወደ ስድስት አመት ቢቆይም ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ነው በ1956 ዓ.ም ወደ አገሩ ለመመለስ የበቃው። ይሁን እና በቆይታው ከብዙ የእንግሊዝ ደራስያን ጋር ለመተዋወቅ በቅቷል። በተለይም ከጆርጅ በርናርድ ሾው ጋር ወዳጆች እንደነበሩ ይነገራል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ የተሰማራው ወደ መንግስት ሥራ ሲሆን በህንድ አገር ዲፕሎማት ሆኖ ከሄደ በሁዋላ ምናልባትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ ኮሜድ ተውኔት «ጠልፎ በኪሴ"ን ደርሷል:: ከዚያ በሁዋላ የደረሳቸው እነ «ያላቻ ጋብቻ»፣ «ጸረ-ኮሎኒያሊስት»፣ «ባለካባና ባለዳባ» የመንግስቱን ስም በኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ካደረጉት ስራዎቹ መካከል ናቸው። በተጨማሪም «The bear» የተሰኘውን እና የታዋቂው የሩሲያ ደራሲ አንቷን ቼኾቭ ተውኔት የሆነውን «ዳንዴዎ ጨቡዴ» በሚል የተረጎመ ሲሆን የጄ.ቢ. ፕሪስትሊን «The Inspector Calls»ን ተርጉሞ ለመድረክ አብቅቷል።

መንግስቱ ከተውኔቱ በተጨማሪም በስነ-ግጥም የተዋጣለት እንደነበር ስራዎቹ ይመሰክራሉ። «የግጥም ጉባኤ» የተሰኘው ስብስብ መንግስቱ የግጥም መክሊት የተቸረው ደራሲ እንደነበር ይመሰክራል። ስዕላዊነቱ ላይ ቢያመዝንም፣ ስልቱም የተለየ እንደነበረ ብዙዎች ይጠቅሱታል፡፡ ካበረከቷቸው ስራዎች 'ያ'ባቶች ጨዋታ'፣ 'የግጥም ጉባዔ'፣ 'ባሻ አሸብር በአሜሪካን አገር' የተሰኙ ግጥም መድበሎች ታዋቂዎች ናቸው፡፡ እንደ መስክርነትም፥ በ1961 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የስነ ጽሑፍ ሽልማት ተሸላሚ፥ በ1962 ዓ.ም ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ተሸላሚም ነበር፡፡

መንግሥቱ ደራሲም ብቻ አልነበረም፤ በተማሪዎቹ የተወደደ መምህር በሳል ተመራማሪ ለባህሉ እና ለቋንቋው ሙት የነበረ ከኢትዮጵያ ብርቅዬዎች አንዱ ነው። በተለያዩ መስሪያ ቤቶችም እየተሸመ በሚገባ ሰርቷል፡፡ ከእንግሊዝ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሲቪል አቪዬሽን 1940 -1950 በኃላፊነት፥ በሕንድ የኢትዮዽያ አምባሳደርነት 1950 -1955 እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በምርምር ማእከል ኃላፊነት 1955 -1962 ያገለገሉት መንግስቱ፥ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ በተቋቋመው የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር "የብሔራዊ ቋንቋ መርሐ ልሣን" መሥራች እና ዋና ፀሐፊ 1962 -1967 ፥ የ‹‹ብሔራዊ ቋንቋ አካዳሚ›› ዋና ፀሐፊ 1967 -1971 በመሆን፥ ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለት ሞታቸው በአ.አ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር መምህርነት በማገልገል በአጠቃላይ - በኢትዮዽያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ እድገት በአማርኛ ሥነ ግጥም ቅኔ እና በቴአትር ድርሰት ተዋናይነት በተመራማሪነት እና በመምህርነት ግምባር ቀደም ሆኖ በነበሩ ኢትዮዽያዊ ባህልና በውጪው ዓለም አዳዲስ ሐሳብ ውህደት ሥርዓት የኢትዮዽያን የሥነ ፅሑፍ ህዋ በብዕር ቀለም አድምቆታል፤ አዳዲስ የቴአትር ጥበባት ባለሙያዎች አፍርቷል።

፫) መሰናክሎች፣ ማለፊያ ጥንካሬዎች

ሰው ነውና እንደልብ ያለ እንቅፋት አይኖርም መቼም፡፡ አብዬ መንግስቱም ታሞ ለንደን ውስጥ ‹ኤጵሶም› በተባለ ሆስፒታል ለብዙ ወራት ተኝቶ እንደነበር አቦነህ አሻግሬ ተርከዋል፡፡ በዚሁ በለንደን ሳለ በአንዲት ኮረዳ ፍቅር መውደቁንና ከለንደኑ አኗኗር ጋር ለመላመድ ከመቸገሩ የተነሳ ትምህርቱን እንኳ በግማሽ ሳያጠናቅቅ መመለሱን ይኼው በቅርበት የሚያውቀው ሰው ይናገራል፡፡

ፖለቲካ ላይ ስምምነት አልነበረውምና በብዙ ተንገላቷል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አመለካከቱ፣ በራስ የመተማመን ልዕልናውና ፍጹማዊነቱ በእጅጉ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ በስነ ጽሑፍ ሥራና በንባብ ፍቅር ተጠምዶም ሌላውን ማኅበራዊ ነገሩን እርግፍ አድርጎት ነበርና ከባለቤቱ የሺ ጋር አልመጥን አለ፡፡ የኋላ ኋላም ተፋታና የሚጠላው ብቸኝነቱን ተያያዘ፡፡ በዚሁ አኗኗሩ አንድ ቀን ሻይ ጥዶ እንቅልፍ ቢያሸልበው ቡታ ጋዙ ተቀጣጥሎ ቤቱን አቃጠለው፡፡

፬) መንግስቱ ለማን አጥተን እንዳናጣው ነገር

አብየ መንግስቱ[1916 - 1980]ን ያጣነው ክህሎትና ክብሩን ሳናውቅለት ነው፡፡ ገና በ64 ዐመቱ፡፡ መንገዱን ዩኒቨርስቲ ገብቶ ቢያስተምረንም ሳንከተልለት ነው ደማሙን ብዕረኛ መንግስቱን ያጣነው፡፡ ከነዚህም መካከል የ‹‹መጽሐፈ ትዝታ - ዘአለቃ ለማ›› ምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ የብዙዎቻችንን አባቶች ሊወክሉልን የሚችሉትን ኢትዮጵያዊ ሊቅ - አለቃ ለማን ታሪክ በራሳቸው አንደበት ያስነበበን እሱ ነው፡፡ የቀደመውም የተከተለውም አለመኖሩ ያስቆጫል፡፡ ‹‹ … የሀገራችንን የመንፈሳዊና የሥጋዊ ባህል ቅርስ በማይነቅዘው መዝገብ ለማከማቸት ታጥቀው የተነሡ እንዳሉ እንዲገፉበት፣ ያልወጠኑትም እንዲጀምሩ ከልብ አሳስባለሁ፡፡›› ብሎ ነበር ደማሙ ብዕረኛ አብዬ መንግስቱ - በመጽሐፈ ትዝታ መቅድሙ፡፡

፭) መርሆች፣ የህይወት ፍልስፍናው

ምልከታው ከፊት ከአባቶቹ ዘመን፣ ከኋላ የልጆቹን ዘመን ያጠናቀረ ነበር፡፡ ዘመናዊነትን ይቀበላል፣ የአባቶቹን ባህል ግን አይተላለፍም ነበር፡፡ የህይወት አካሄዱን ልብ ብለን ያስተዋልን እነደሆነ፣ ፊት ለፊት ራሱን ለአደጋ የሚያጋፍጥ ሳይሆነ በጨዋታ እያስመሰለ የሚሸነቁጥ ዋዘኛ መሳይ ሰው ነበር፡፡ ለዚህም እንደምሳሌ የሚሆነን ራሱ ‹‹ባሻ አሸብር በአሜሪካ››ን ባነበበት ምሽት በመግቢያው የተናገረው በቂ ነው፡፡ ቴአትሮቹን ስናይ ከርዕሳቸው ጀምሮ ለሳቅ ብቻ የተገዘቱ ይመስላሉ እንጂ ሁሉም መልዕክት አዘል ነበሩ፡፡ መንግስትን፣ ባህልን፣ ከበርቴዎችን፣ ህዝብን የሚተቹ ነበሩ፡፡ ፊት ለፊት እንደ ጉዱ ካሳ ሳይሆን በጎድን እንደ ፊታውራሪ አካሉ(‹ፍቅር እስከመቃብር›ን ያነበቡ ይሄ ምሳሌ ይግባቸው) ነበር ትችቱ፡፡

ለመሰናበቻ ራሱ አብዬ የጠየቀውን በራሱ አፍ ጠይቀን እጅ እንነሳለን፡፡

‹‹ምንድን ነው ሰበቡ…

ለምንድን ነው አልኩኝ፣ ለምን ምክንያት፤

ይህ ዓለም መኖሩ አዱኛ ህይወት፣

ህጻን መወለዱ አርጅቶ ሊሞት፣

ለምንድን ነው አልኩኝ ለምን ምክንያት?››

ምንጮቻችን

1. ደማሙ ብዕረኛ - ግለ ታሪክ፣ በመንግስቱ ለማ፣ ሜጋ አሳታሚዎች፣ 1988ዓ.ም.

2. መጽሐፈ ትዝታ - ዘአለቃ ለማ ኃይሉ፣ መንግስቱ ለማ እንደጻፈው፣ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት፣ ፲፱፻፶፱ዓ.ም

3. www.addisadmasnews.com፣ Saturday, 24 January 2015

4. አቦነህ አሻግሬ -- ብሌን መጽሔት፣ ቅጽ1 ቁጥር 1



አስተያየት እዚህ ያስቀምጡልን

ስም [*]ትክክለኛ ሰዉ መሆንዎን ያረጋግጡልን [*]አስተያየት እዚሁ ያስቀምጡልን


እስካሁን (3) አስተያየቶች ተሰጥተዉበታል


 Habtamu     2019-05-07
it is good


 ስም ያልጠቀሰ     2015-11-04
Liked


 Tadele Ayalew     2015-10-28
The author of many books, stage plays and teacher of many artists, Mengistu Lema-Gashe!

መንግስቱ ለማ

የአባቱ ልጅ፣ ቁርጠኛውና ኢትዮጵያዊውን ጸሐፌ ተውኔት፤ ለዚህ ዕትም መርጠንላችኋል፡፡

መንግስቱ ለማ
Read in PDF 2015-10-27 በምሳሌ ዋለ


ከዚህ ቀደም ግለ ታሪካቸዉን ካቀረብንላቸዉ መካከል

እጅግ የተከበሩ የዐለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የእኔን ሥራ የሚያዩ ሁሉ ተስፋ እንዲያገኙ፣ ስለኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪቃ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው፣ በፀሐይ ጮራ እንዲሞቁ፣ ከሁሉም በላይ ግን “ይቻላል” የሚል እምነት እንዲኖራቸው ፍላጎቴ ነው
እጅግ የተከበሩ የዐለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ Read in PDF

ሊቁ ልበ ሙሉ ነበሩ፡፡ ኃይማኖተኛና ‹ዛሬ ከጨለመብን ይልቅ ነገ የሚበራልን ይበልጣል› ባይ ተስፈኛም ነበሩ፡፡ ዋጋ ቢያስከፍላቸውም ራሳቸውን የሚያከብሩ ክቡር ሰው ነበሩ፡፡ ተጨማሪ ያንብቡ



ተሥፋዬ ገሠሠ ለሁሉም ጊዜ አለዉ
ተሥፋዬ ገሠሠ Read in PDF

“የወፍ ወንዱ፣ የፖለቲከኛ ሆዱ አይታወቀምና ሁሉን በብልሀት ያዙ” የሚል ምክር ከአፋቸዉ ተጨማሪ ያንብቡ



ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ኢትዮጵያ ባንተ አልተጀመረችም ባንተም አትጠፋም፣ ትቀጥላለች!
ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ Read in PDF

ከተያያዘው ፋይል ተጨማሪ ያንብቡ



ብላቴን ጌታ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ፡፡
ብላቴን ጌታ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን Read in PDF

የማይድን በሽታ ሳክም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የሰው ሕይወት ስከረክም
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም።
የጋሽ ጸጋዬን ህይወት ከዚህ በላይ የሚገልጸው ቃል የለም(አራት ተጨማሪ ያንብቡ


መልእክተ የሓ

በዚህኛዉ ዐምድ ታሪካቸዉ እንዲቀርብ የምትፈልጓቸዉን ሰዎች እንድትጠቁሙን ወይም ደግሞ የተጻፈ ታሪካቸዉ ካለዎ በዚህ በኩል ቢያገኙን ደስታዉን አንችለዉም፡፡

መገኛችን

ለገሀር፣ አዲስ አበባ

19686

yehaarts@gmail.com

+251 912 944937

ጉርሻ - Bonus

“ከፊደል ሀ፣ ከከተማ የሓ የሚቀድም የለም” ተብሏል፡፡ የአጋዝያን ምድር፣ የግዕዝ ቋንቋም መነሻ፣ የልዕልናችንም መጀመሪያ ነበረች፡፡ በብዙ ጥበብ የተንበሽበሽች፡፡ አሁን እምብዛም ሞቋት የማታድረዋ የሓ፤ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሁነኛ ዋና ከተማ ነበረች።

(2015-2024) © yehaarts