“ፍቅሪ” አለኝ፣ እንዳይነጋ የለም እድሜ ልክ ያከለብኝ ጨለማ አልፎ ረፋዱ ላይ ስልክ በመደወል።
“ሙልዬ? የኔ ጌታ! … አለህልኝ ሙሌ? አለህልኝ ወይ?” ጉልበቴ ግዉ እስከሚል ድረስ ወድቄ መሬቱን ጨምጭሜ ሳምሁት። ደስታዬ የሚያደርገኝን አሳጣኝ። ዘልዬ ሰማዩን ብስመዉ እንኳን የልቤ መድረሱን እንጃልኝ። ተመስገን! በሕይወት አለ ማለት ነዉ? በአዛኚቱ! እኔማ ስንቱን ነበር ያሰብሁት? በዚያ ላይ ስልኩ ጭምር ዝግ ሆኖብኝ በጭንቀት ልሞት ነበር። ሥራዉም በጸባዩ ብዙ ጊዜ ከብዙ አይነት ሰዎች ጋር ስለሚያዳርሰዉ፣ ክፉ ክፉዉን ብቻ እያሰብሁ እንዲችዉ ስነፈርቅ እና ስንጨዋለል ነዉ ያደርሁት። እንዲያዉ አደርሁ አልሁት እንጂ እንደዋዛ፣ አዳሬስ አዳርም አይደል።
“በደህናህ ነዉ ግን?” አልሁት፣ ወደ ነፍሴ ለመመለስ ዐይኔን ጨፍኜ እየገለጥሁ።
“ምነዉ?”
“እህእ… ምነዉ ትለኛለህ እንዴ ደሞ?”
“ምነዉ ፍቅሪ?”
“ኧረ ሙሌ በማርያም! ጭራሽ መቀለድ ሁሉ ያምርሀል? ይልቅ ንገረኝ፣ ምን ገጥሞህ ነዉ?”
“እራት ምናምን ተባብለን ነበር እንዴ ፍቅሪ?”
“ረስቸዉ ልትለኝ?”
“አይገርምሽም ረስቼዋለሁ”
“ኧረ እንዳታስቀኝ”
“አንቺን ይንሳኝ! ምን አይነት ከንቱ ነኝ በናትሽ? እንዴት ረሳሁት ግን? ለነገሩ ባልረሳዉ ነበር የሚገርመኝ እንዲያዉም። ያዉ ሥራዬን ታዉቂዉ የለ? የትናንትናዉ ደግሞ የተለየ ነበር። ብታይኝ ትንፋሼን እንኳን እንደልቤ የምተነፍስበት ፋታ አልነበረኝም። ያ ከጀርመን እያስመጣሁት ነዉ ያልኩሽ እቃ… ስለሱ አልነገርሁሽም ወይ ፍቅሪ? ነግሬሻለሁ ኧረ።… አዎ፤ እሱ እቃ ሊስተጓጎልብኝ ሲል አይገቡ ገበቼ ነዉ ለትንሽ ያተረፍሁት ብታይ። ደስ አይልም?”
“ተመስገን! እዉነት በደህናህ ነዉ?”
“ኮራሽብኝ ኣ ፍቅሪ?” አለኝ፣ ረዥሙን የእፎይታ ትንፋሼን እየደጋገምሁለት ሳለ። “ምናለ በይኝ ኋላ… ክብረት የሚሏት ነገር መድረሻ ሰማይ ካላት፣ በዚያች ሰማይ ከእኔና ከአንቺ ቀድሞ ማንም አይደርስባትም። እኔና አንቺ ብቻ! ያኔ ነዉ እኛን ማየት። መነኩሴዎች ጭምር የሚቀኑበትን ሠርግ እናሠርግና፣ ሥፍር ቁጥር በሌላቸዉ ልጆች ቤታችንን ሞልተን… ይታይሻል ኣ ኑሯችን?”
“ይሁን”
“‹ይሁን›? ምነዉ ፍቅሪ፣ አላመንሽኝም እንዴ?”
“እህእ… አሁን አለማመንን ምን አመጣዉ እዚህ? አንተን የማምነዉን ያህል የፈጠረኝንስ አምነዋለሁ እንዴ? ተዉ እንደሱ አትጠይቀኝ እንጂ ሙሌ”
የምሬን ነዉ፤ በሰማይ በምድሩ እንደሱ የምተማመንበት የለኝም። በእኔ ቤት ሀይማኖተኛ ተጨማሪ ያንብቡ
1 ከ 7