፩) ትውልድ(ቀንና ቦታ)፣ ቤተሠብ፣ ትምህርት
ኦሮሚያ - አምቦ አካባቢ ቦዳ የምትባል ተራራማ ቦታ አለች። ጣልያን ልትገባ ሠሞን፤ ትውልዷ ከአንኮበር ከሆነችው እናቱ ፈለቀች ዳኜ እና ትውልዱ የመጫ ኦሮሞ ከሆነው አባቱ ሮበሌ ቀዌሳ - ጸጋዬ (ጸጋዬ ሮበሌ - ሮበሌ ቀዌሳ - ቀዌሳ ደበል - ደበል ዳና - ዳና አዋዲ - አዋዲ ዳንዳዎ - ዳንዳዎ ሲናን - ሲናን ጂዳ - ጂዳ ኢላሙ - ኢላሙ ቦናያ) ተወለደ። ሐምሌ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም። አባቱ ሮበሌ ከጸጋዬ መወለድ አበክሮ የዐለም ስሙን በክርስትና ስሙ ሽሮ ገብረመድኅን ተባለ። ገብረመድኅን ቀዌሳ፣ ለጣልያኖች የልብ ዉጋት ለሆኑት አርበኞች ተባባሪ ነበርና ጸጋዬ በጨቅላነቱ ወደ ጎሮምቲ ከናቱና ከእህቶቹ ጋር ሄደ። የእናቱ ዘመዶች የሆኑት ካህናትም ጣልያንን ሽሽት ከአንኮበር ወደ ጎሮምቲ መጥተው ተቀላቀሏቸው። ጸጋዬም ፊደል የመቁጠርና ግዕዝ የመማር እድሉን ከእነሱ አገኘ። የአባቱ ወንድም ሰቦቃ ቀዌሳ ደግሞ የኦሮሞ ገዳ ሥርዐትና ባህል አስተማረው።
ከጎሮምቲ ወደ አምቦ በመሄድ ዘመናዊ ትምህርት ሊማር ጣልያኖች ከፍተውት በነበረው ት/ቤት ገባ። ጣልያኖች ሲወጡ ወደ አምቦ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛወረ። ስምንተኛ ክፍል ሲጨርስ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት ተዛወረ። ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጦ ወደ ንግድ ሥራ ት/ቤት ገብቶ በዚሁ ተመረቀ። በኋላም በቺካጎ ብላክስቶን በህግ ትምህርት ተመርቆ በ1952 እንደ ወጣ በለንደን ከተማ የቴአትር ትምህርት በሮያል ኮርት ቴአትርና በፓሪስ ኮሜዲ ፍራንሴዝ ተከታትሏል።
በ1990 ለጉበት በሽታ ሕክምና በመሻት ወደ ማንሃታን በሄደበት አርፏል። እናም፣ በአዲስ አበባ በስላሴ ቤተክርቲያን ተቀበረ።
፪) ሙያ፣ አስተዋጽዖ፣ ተሰጥዖ
ክብረ ብዙው (ሎሬት፣ ብላቴን ጌታ፣ ባለቅኔ፣ ፈላስፋ፣ ጸሐፌ ተውኔት) ጸጋዬ ገ/መድኅን አምቦ ሳለ ‹‹ንጉስ ዳዮኒሰስና ሁለቱ ወንድሞቹ›› የተባለ ቴአትር ጽፎ ሲያቀርብ ጃንሆይ ባጋጣሚ ተገኝተው ‹አጀብ› ብለውት ነበር። በ1949፣ የ16 ዐመት ልጅ ሳለ። በኋላም ንግድ ሥራ ት/ቤት ሳለ የጣልያንን ወረራ ወቀሳ ‹‹የደም አዝመራ›› ብሎ ቴአትር በወላጆች በዐል አቀረበ። እያደር፤ ‹‹Oda Oak Oracle›› (በ1957- በእንግሊዝኛ - ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ታትሞ በተላያዩ አገሮች ተመድርኳል)፣ አዝማሪ(በ1967 - በእንግሊዝኛ - በለንደን ኤንደንበርግ ታትሟል)፣ ‹‹ቴዎድሮስ››(በ1960)፣ ‹‹Collision of Altars››(በ1961 - በስድስተኛው ክ/ዘመን በካሌብ ዘመን የነበረችቱን ኢትዮጵያ ገልጦበታል)፣ ‹‹ሌላው አዳም››(በ1944 የንግድ ሥራ ት/ቤት ሳለ) ፣ ‹‹የሾህ አክሊል››(በ1952)፣ ‹‹ጆሮ ደግፍ››(1952- በቀድሞው ቀ/ኃ/ሥላሴ ቴአትር ቀርቦ በሳንሱር ተጠይቆበት ነበር)፣ ‹‹አስቀያሚ ልጃገረድ››(በ1952)፣ ‹‹በልግ››(በ1950)፣ ‹‹የከርሞ ሰው››፣ ‹‹ኦቴሎ››(በ1957- ከዊልያም ሼክስፔር ሥራዎች አዛምዶ የተረጎመው)፣ ‹‹ንጉስ ሊር›› (በ1961 - ከዊልያም ሼክስፔር ሥራዎች አዛምዶ የተረጎመው)፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሠዐት››፣ ‹‹ማክቤዝ›› (1961 - ከዊልያም ሼክስፔር ሥራዎች አዛምዶ የተረጎመው)፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››(በ1966)፣ ‹‹እናት ዐለም ጠኑ››(በ1966)፣ ‹‹ዚቀኛው ጆሮ›› (በ1977 - በአበራ ጆሮ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ቅኔ ለበስ ቴአትር፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ በኢሠፓ አዳራሽ ቀርቦ ታግዶበታል)፣ ‹‹ምኒልክ›› (በ1982 - ታሪካዊ)፣ እና ከቁጥር የበዙ ስራዎችን በዋናነት በጸሐፌ ተውኔትነት ሲልበትም መራሔ ተውኔት ሆኖ አጉርፏል።
ጋሽ ጸጋዬን በጸሐፌ ተውኔት ክህሎቱ ልዩ የሚያስብለው ብዛቱ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የገጸ ባህርያቱ ዉክልና፣ የመድረኩ ተምሳሌትነት፣ የቃለ ተውኔቱ ትርጉመ ብዙነት፣ የታሪክና የስነ ልቦና ገብነታቸውም ጭምር እንጂ። ብዙ ስራዎችን የተወነው ታዋቂው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም እንዲህ ሲል ገልጾታል፡- ‹‹የጋሽ ጸጋዬ አተራረክ ቀድሞ ለመገመት ይቸግራል። ‹እሠይ እነገሌን ልክ ልካቸውን ሊነግርልኝ ነው› ስትል ሁለት መንታ አድርጎህ ባልጠበከው መንገድ ይሸውድሃል።… ››
ሌላው አቢይ ሙያው ባለቅኔነት ነው። ሁሉም ሰው የሚያውቀው ‹‹እሳት ወይ አበባ›› መጽሐፉ ላይ የተካተቱትን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች እና አጋጣሚዎች ሁሉ ያቀረባቸው እንደ አሸን የፈሉ፣ እንደ ቅኔ የሚያመራምሩ፣ እንደ መሪ የሚመሩ ግጥሞች አሉት። በተለየ ሁኔታ የራሱን የግጥም ስልት(ጸጋዬ ቤት) የፈጠረ ብዕረ ብርቱ ሰው ነበር።
ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር በተለያዩ ኃላፊነት ያገለገለ ሲሆን፣ ገና በወጣት እድሜው የቀድሞውን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት ያሁኑን ብሔራዊ ቴአትር ቤትን በስራ አስኪያጅነት መርቶ ነበር። ባንድ ወቅት የቀዳማዊ ሽልማት ድርጅት እጩ በመሆን የ7 ሺ ብር የወርቅ ኒሻንና ዲፕሎማ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
፫) መሰናክሎች፣ ማለፊያ ጥንካሬዎች
‹‹በሥስተኛው ዐለም ውስጥ የብዕር ግድያ ብቻ ሳይሆን የሞራል ግድያ አለ›› የሚለው ጸጋዬ፣ በ፲፱፻፶፫ዓ.ም የሠራው ‹‹ጆሮ ደግፍ›› ቴአትር ለእስር ዳርጎት ነበር። በደርግ ጊዜ ደግሞ በ‹ጋሞ› እና ‹አቡጊዳ› ቴአትሮቹ ተቆንጥጦባቸዋል። የስድስት ወር ደሞዝ የተከለከለበት ጊዜም ነበር።
ጋሽ ጸጋዬን በጠና ሳያውቁት በዝናው ብቻ የሚያከብሩትን ያህል ነቃፊዎችም ነበሩበት። ችሎታውን ልባቸው እያወቀው እንኳን ብርቱ ጸሐፌነቱን የሚክዱት ቀላል አይደሉም። ከሞተ በኋላ እንኳን ፋንታሁን እንግዳ የተባለ የቴአትር ባለሙያ ክብሩን እንዲህ ባዶ አስቀርቶታል፡- ‹‹…ጸጋዬ በአደባባይ ሲታዩ የተደናቂ ደራሲ ስብዕና ተላብሰው ነው የሚታዩት። ከአደባባይ በስተጀርባ ደግሞ ፖለቲካዊ ስብዕና ነው ያላቸው። ተንሾካሿኪነት ይወዳሉ። …››(‹‹ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ›› ገጽ 569)። ይኸው ሰው በዚሁ መጽሐፍ ላይ ለጸጋዬ የተሠጠው ክብር ጸጋዬ በተንኮልና በብልጠት ያገኘው እንደሆነ፣ ምንም አይነት ክብር(ሎሬት፣ ብላቴን ጌታ፣ …) እንደሌለው ደጋግሞ ገልጧል። ሥራዎቹም ብዙ ጊዜ ለመድረክ ይበቁለት የነበረው ከባለስልጣናት ጋር በሚያደርገው መጨማጨም እንጂ ከሥራዎቹ አንዱም እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ዋቢዎችን ለመጥቀስ ሞክሯል።
እኛም ስለወደድነው ብቻ ፍጹም ነበር ለማለት ባንደፍርም፤ እዚህ ላይ አንድ ተረት መደስኮሩ አይከፋም።
(በቀድሞው ጊዜ ነው አሉ። የቆሰሉ ወታደሮች የወዳደቁበት አካባቢ የሚያልፉ ጓድ ሁሉም ሰው እንደ ሞተ ለሃኪሞች ‹ሪፖርት› አደረጉ። ሃኪሞችም አሜን ብለው ጋዎናቸውን አወለቁ። ከወዳደቁት ቁስለኞች ግን አንዱ በህይወት ነበርና ቀና ብሎ ‹‹እርዱኝ›› ሲል ተማጸነ። ሃኪሞቹ ግን አይናቸው እያየው፣ ጆሯቸው እየሰማው፤ ‹‹የለም ሞተሃል›› ብለው ካዱት። ‹‹ኧረ አለሁ እርዱኝ›› ቢላቸው ‹‹ማን ስለሆንህ!? ከጓድ እከሌ አንተን እንመን? ሞተሃል ሞተሃል ነው!›› ብለውት ሄዱ ይባላል።) እንደ ፋንታሁን እንግዳ ያሉ ሰዎችም ያሉን እንዲህ ነው። ‹‹እነከሌ እነከሌ ‹የጸጋዬ ስራዎች ተልካሻዎችና እርባና ቢስ ናቸው› ብለዋና በግዳችሁ እመኑ!›› እኛና ሌሎች ግጥሞቹን ያነበብን፣ ቴአትሮቹን የታደምን እና ስራዎቹ የገቡን ሁሉ ክብሩ የእውነት ይገባዋል እንላለን። ያውም ባያንሰው!
፬) ብላቴን ጌታ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅንን አጥተን እንዳናጣው ነገር
ብዙዎቹ ቴአትሮቹ ላይ ያሉት እያንዳንዱ ነገሮች ምሳሊያዊ(Symbolism) ነበሩ። በዚህ ስልቱ ወደር የማይገኝለት ቢሆንም ጋሽ ጸጋዬን አጥተን ያጣነው ግን ይህን ብቻም አይደል። የቋንቋ ዉበቱ፣ የታሪክ እውቀቱ፣ የፍልፍናው ልክ፣ … ማን ነበር እንደሱ? የሀገራችንን ትውፊታዊ ዜማዎችን፣ እንቆቅልሾችን፣ ተረትና ምሳሌዎችን፣ ትላልቅ ሃሳቦችን በሚገባ ያውቃቸዋል፣ በተውኔቶቹም የክብር ቦታ ነበራቸው። ዛሬስ?
፭) መርሆች፣ የህይወት ፍልስፍናው
የማይድን በሽታ ሳክም
የማያድግ ችግኝ ሳርም
የሰው ሕይወት ስከረክም
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም።
የጋሽ ጸጋዬን ህይወት ከዚህ በላይ የሚገልጸው ቃል የለም(አራት ነጥብ)።
ምንጮቻችን
፩) ምስጢረኛው ባለቅኔ (ሚካኤል ሽፈራው፣ ህትመት ፋር ኢስት ትሬዲንግ፣ ፳፻፮ዓ.ም)
፪) ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ (ከገጽ 560-569)(ፋንታሁን እንግዳ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ ፳፻ዓ.ም.)
፫) www.tsegaye.se (የጸጋዬ ቤት፣ )
፬) ማዕቀብ (ከገጽ 45)(እንዳለጌታ ከበደ፣ HY Int. printing press ታኅ ፳፻፮)
፭) ታሪካዊ ተውኔቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ ፳፻፫ዓ.ም)
አስተያየት እዚህ ያስቀምጡልን
እስካሁን (5) አስተያየቶች ተሰጥተዉበታል
Habtamu 2018-08-14
Shega sew norual
ፍፁም እንዳለ 2016-07-24
እናመሰግናለን
Minabu Baye 2016-06-03
ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ፡፡
Minabu Baye 2016-06-03
Thank you, Yeha!
እንዳለ ባያብል 2016-06-03
እውነትም ባለ ቅኔ!