“ግለጠዉ”
“ጭራሽ ለእኔ ነዉ ያመጣሽዉ?”
“አዎ፤ አንብበኸዋል ኣ?”
“ኧረ እኔ እንኳን ላነበዉ፣ እንዲህ የሚሉት መጽሐፍ መኖሩንም ከነጭራሹ አላዉቅም። መጽሐፈ እርግማን? ሆ! ከየት አመጣሽዉ?”
“ከዚያዉ”
“ከየት?”
“ከዚያዉ ከትናንትናዉ ስፍራ”
“ከትናንትናዉ?”
“ትናንትና እንዲህ ሆነን ተቀምጠን አልነበር?” ብላ ጀመረች፣ ያን እጇን ወደ ታች እየሰደደችብኝ። አቤት መከራዬ! ምን ልትሆን ነዉ ደግሞ?
“በእናትሽ!” አልኋት። በእናቷ! እሷ እጇን ዝቅ ያደረገችብኝ እንደሆነ፣ የምሆነዉን አላዉቅም። ገላዬን ይቅርና ልብሴን ብትነካዉም መቅለጤ ነዉ። በእናቷ እንዳትነካኝ። ይኼም አልበቃት ብሎ እኮ፣ እሷ ለራሷ ዐይኖቼ የምትላቸዉ ለእኔ ግን እሳት የሆኑ ነገሮች አሏት። ኧረ በእናቷ! እንዳታየኝ። በቃ ሙሽሽ - ቅልጥ - ጭልጥ ብዬ ማለቄ ነዋ! ትናንትና እንዲሁ የማይታይ ነገሬን አይታብኝ፣ አሜን አሜን ስል ነዉ ያመሸሁላት። ነገረ ሥራዋ ሁሉ ጋን ሙሉ እንደጨለጠ ስለሚያሰክር፣ የሆንሁትን አላስታዉስም። ብቻ ሳልዘላብድ አልቀረሁም።
“ለአበዋ እኮ ነገርሁት” አለች።
“ምኑን?”
“እህእ! የመስቀል እንደምንጋባ ነዋ”
እርፍ! ጭራሽ? ቆይ ከማን ጋር ነዉ የምትጋባዉ? ስለ ጋብቻ አዉርተናል ማለት ነዉ ግን? ጭራሽ ቀን ሁሉ ቆርጠናል? ያዉም የመስቀል!
“ምን አስቸኮለሽ?” አልኋት፣ የምለዉ ቢቸግረኝ።
“ማለት? አበዋ እኮ ነዉ። ከዚህ ወዲያ ምን ቀረን? መስቀል እኮ ደረሰ። አሁን ካልነገርሁት፣ መስቀል ካለፈ እንድነግረዉ ነበር እንዴ ሐሳብህ? ወይስ እንደ ልማድህ አሁንም ሸንግሎ ማለፍ አማረህ?”
“ኧረ እኔ”
“ሞክረኛ! በል ሞክረኝ። መጫወቻህ እንደሆንሁ ሞክርና አሳየኝ”
“ቆይ”
“ባታስበዉ ነዉ የሚሻልህ! በጭራሽ!”
“እስኪ ቆይ”
“አሜን ብሎ ወደ ኋላ አላዉቅም። አንዴ ነዉ የጨረስነዉ። ከገባኸዉ ቃል አንዲቷም ከምትጎድል፣ ሚስማር ላይ ብትቆም ይሻልሃል። ወደ'ኔ እንድትመጣ ያደረግሁትን አላዉቅም፤ የምትሄድ ከሆነ ግን አይቀናህም። ምናልባትም ከእኔ በፊት የነበረችዋ፣ “ብቻ ደህና ሁንልኝ እንጂ” ብላ የልብ ልብ ሰጥታ ሸኝታህ ይሆናል። እኔ ላይ ግን አይሰራም፤ እንዳታስበዉ! እንዲያዉም ጨርሼ ልንገርህ ኣ? አጣድፈህ አጣድፈህ እዚህ አድርሰኸኝ ስታበቃ፣ ይቺን ታህል እርምጃ በሸሸኸኝ አፍታ ነዉ በአጭር እንዲያስቀርህ ለመጸለይ የምንበረከከዉ። ከእኔ ዘወር ብለህ ወደ ሌላ የተራመድህ እንደሆነ፣ የፈላ ጎረፍ ደርሶ እያዳፋ እንጦሮጦስ ያግባህ! እኔን ያቀፉ እጆችህ ሌላ የሚያቅፉ ከሆነ፣ ገላዋ የገሀነሙን እሳት ይሁንብህ። ከንፈሮቼን የሳሙ ከንፈሮችህ በሌላ የሚረጥቡ ከሆነም፣ የሰራ አከላትህን እከክ አንድዶ ያንገብግብህ! ሌላ ነገርህም ሌላ ያማረዉ እንደሆነ፣ ሰማያዊ ዛፍ ቆራጮች ወርደዉ ከስሩ ይንቀሉብህ! ሰማያዊ መጥረቢያ በከሃዲ ገላህ ይለፍ!”
“መስቀል ዛሬ በሆነና በተጋባን” ብዬ ላቋርጣት ስል፣ ይኼን የምልበት ፋታ እንኳን ሳትሰጠኝ ቀጠለች።
“እኔ እሺ ያልሁህን ሁሉ እሺ ብዬሃለሁ። መቼም አልለወጥብህም። ካደረግሁትም በእኔ ይሁንብህ”
፧
www.yehaarts.com
አስተያየት እዚህ ያስቀምጡልን
እስካሁን (0) አስተያየቶች ተሰጥተዉበታል