ገ ረ ገ ራ     በማንኛዉም የመጽሐፍ አዟሪና መደብር ይገኛል።     Order4Delivery (እዚሁ ያዝዙ)
ቃለ ምልልስ

በዚህኛዉ ዐምድ፣ በጥበብ ተሞክሯቸው የቀደሙ አንጋፋዎችና ወጣቶች ለቃለ ምልልስ ይጋበዙበታል

፩) ትውልድ(ቀንና ቦታ)፣ ቤተሠብ፣ ትምህርት

የሓ፡- የቤታችን የመጀመሪያ እንግዳችን ለመሆን ስለፈቀድህ ክብር ይስጥልኝ በቅድሚያ፡፡

ዲ/ን፡- እኔም ደስ ብሎኛል፡፡

የሓ፡- የት አካባቢ ነው ትውልድህ ግን?

ዲ/ን፡- የተወለድኩት ደሴ ነው፡፡ ያደግሁት ባ/ዳር ነው፡፡ የምኖረው ደግሞ አዲስ አበባ ነው፡፡

የሓ፡- ባለቤትህ ማን ትባላለች?

ዲ/ን፡- ጽላት ጌታቸው ትባላለች፡፡ እውነት ለመናገር እሷ ባትኖር ኖሮ ደግሞ አሁን የሆንኩትን 75 በመቶውን እኔ አልሆንም ነበር፡፡ ለበጎ ነገር ቀስቃሼ እሷ ናት፡፡ በያገሩ ስዞር ሁሉ፣ ስራዬ ሲበዛ ሁሉ፣ ወጭዬ ሲበዛ ሁሉ እሷ ስላለች ነው ያልከበደኝ፡፡

የሓ፡- በዚያው ደግሞ ስለ ልጆችህ ንገረኝ፡፡ ስንት ናቸው? ትንከባከባቸዋለህስ በሚገባ?

ዲ/ን፡- ሦስት ናቸው፡፡ እንክብካቤማ የግድ ይላል፡፡ እኔ ለቤቴ ጊዜ አለኝ፡፡ ወይ ካገር ካልወጣሁ ወይም ክፍለ ሀገር ካልሄድኩ በቀር ሁሌም ቅዳሜ እቤት ከቤተሰቦቼ ጋር ነኝ፡፡ እንዲሁም ሰርክ ጉባዔ ከሌለኝ በቀር በጊዜ ነው ወደ ቤቴ የምገባው፡፡ በተለይ ለአንድ ለኹለት ሳምንት ያህል የእረፍት ጊዜ ሲኖራቸው በተቻለ መጠን አብሪያቸው እሆናለሁ፡፡ እና ለቤቴ የመደብኩትን ነገር የተለየ ጉዳይ ካገጠመኝ በቀር አሳልፌ አልሰጥም፡፡

፪) ሙያ፣ አስተዋጽዖ፣ ተሰጥዖ

የሓ፡- የስራህ ብዛት ይታወቃል መቼም፡፡ የሃይማኖት መምህርነቱ አለ፣ ልጅ ታሳድጋለህ፣ ሰዎችን ታማክራለህ፣ መጽፎችን ትጽፋለህ፣ ጥናቶችን ታጠናለህ፣ የ‹አግዮስ ህትመት› ስራ አስኪያጅ ነህ፣ ካገር አገር ከክልል ክልል ትዞራለህ … ጊዜው ላንተ ይበዛልሃል ልበል?

ዲ/ን፡- ለእያንዳንዱ አዋዋሌ መርሐ -ግብር ስላለኝ ይመስለኛል፡፡ ነውም ደግሞ፡፡ ሰዎችን ለማማከርም ቀን መድቢያለሁ፡፡ ለሌላውም እንዲሁ ሰዐት ቆርጨለታለሁ፡፡ እንጂ እንዳልከው አልፎ አልፎ ሰበር የሚገቡ ‹ፕሮግራሞች› አሉ፡፡ ከመንግስት የሚመጡ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች የሚመጡ፣ ከዐለም አቀፍ ድርጅቶች የሚመጡ፣ ከሃይማኖት ተቋማት የሚመጡ በጣም ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ እንደጠቃሚነታቸውና እንዳስቸኳይነታቸው ከመደበኛ ተግባሮቼ ጋር አስተያያለሁ፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ሰዐቱ ከበቂም በላይ ነው፡፡

የሓ፡- የበጎ ሰው ሽልማት ዘንድሮ አልዘገየም?

ዲ/ን፡- ዘግይቷል፡፡ የዘገየው ግን በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው የምርጫው ነገር ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ በመሀል ያጋጠመን በሊቢያ የሆነብን ሃዘን ነው፡፡ በሁለቱ ኩነቶች መካከል ሽልማቱ ዘገየ፡፡ ነገር ግን አሁን እየመጣ ነው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት እጩዎቹ ታውቀው ይገለጡና ዋናው ሽልማት ነሐሴ ወር ማብቂያ ላይ ይካሄዳል፡፡

የሓ፡- ሦስት ድኅረ ገጾች አሉህ፡፡ ‹የዳንኤል ክብረት እይታዎች›፣ ‹አግዮስ› እና ‹የበጎ ሰው ሽልማት› የሚሉ፡፡ በተለይ ኹለቱን የመጎብኘትህ ነገር ግን ቀዝቅዟል፡፡ አንዱስ አይበቃህም ነበር?

ዲ/ን፡- ሦስት የሆኑ ለሦስትነታቸው ነው፡፡ የተለያየ ነው ስራቸው፡፡ እንዳልከው ግን አግዮስ ብዙም አልተከታተልኩትም፡፡ ያ የሆነበት ምክንያትም በ‹ቴክኒክ› ክፍተት ነው፡፡ በቅርቡ ግን ሦስቱም እንደጠባያቸው እንጠቀምባቸዋለን፡፡

የሓ፡- ክርክሮች በኛ አገር ከታች ናቸው ብዙውን ጊዜ፡፡ ‹‹እገሌ ለምን በእንግሊዝኛ ቴንኪው አለ?›› ‹‹እገሌ ለምን ሱሪው ጠበበ?›› አይነት ናቸው፡፡ የእውነት ለውጥ ለማምጣት ክርክራችን እንዲህ ነው መጀመር ያለብን? ምክንያቱም፤ አንደኛ አሁን ከኢትዮጵያዊነት የጎደሉብን ነገሮች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ ደግሞም እነዚ ዉጤቶች ናቸው፡፡ እንግሊዝኛ የመቀላቀላችንም፣ ሱሪ ዝቅ አድረገን የመታጠቃችንም፣ የውጭ ነገር የመውደዳችንም፣ ወደ ውጭ የማየታችንም ሁሉ ምክንያት ምን እንደሆነ ብንሟገት አይሻልም? ዋነኛ መነሻ መከራከሪያችን ሊሆን የሚገባው ነገር ምን ነበር ትላለህ?

ዲ/ን፡- አንደኛ የክርክር ባህላችን የት ድረስ ነው? በእርግጥ የገጠሩ ሰው የራሱ የክርክር መንገድ አለው፡፡ ከተሜዎቹና ዘመናዊዎቹ ደግሞ ምን ያህል የክርክር ባህል አለን ስትል ያን ያህል ይሆንብሃል፡፡ ባለፉት ሦስት ስርዐቶች ድጋፍና ተቃውሞ እንጂ ክርክር ብዙም ቦታ የለውም፡፡ ስለዚህ ያደገ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አርባ አመት ሙሉ ገጠር ኖሮ ወደ ከተማ ሲገባ የህጻን መጫዎቻ ቢያይ ይጓጓል፡፡ ለምን አርባ አመት ሙሉ ያላየውን ስላየ፡፡ ስለዚህ ከልጁ እኩል ነው ያንን መጫዎቻ ያየው፡፡ እኩል ነው የሚያየውም፡፡ እኛም እንዲሁ ነን፡፡ ስላልሄድንባቸው እንግዳ ይሆኑብናል፡፡ መከራከሪያ ርዕሳንም ከታች መጀመሩ አይደለም ክፋቱ፡፡ አለማደጉ እንጂ፡፡ ወደጣሪያው አለመሄዱ ነው ክፋቱ፡፡ ሁልጌዜ እንዲህ የምንዋቀሰውም ለዚሁ ነው፡፡ ዛሬም ‹‹ለምን እከሌ ሲያወራ እንግሊዝኛ ቀላቀለ!?›› እንላለን፡፡ ነገም፡፡ ወደ ላይ አላደገም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዳበረ ነገር አለ ቢባል የቀብር ስነ ስርዐት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥሩንባ ሲነፋ ቀጥሎ ምን እንደሚለፈፍ ይገባናል፡፡ ነጠላ ዘቅዝቆ መሄድ ምን እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ልባችን ሞልቶ ማኅበረሰቡ ላይ ሰርጓል የምንለው እሱን ብቻ ነው፡፡ ክርክሩ ግን እንዲያ አልሄደም፡፡

የሓ፡- ምሳሌዎችን ስትመስልና ስነቃል ላይ ያለህ እውቀት የሚገርም ነውና ከየት መጣ?

ዲ/ን፡- እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ እዞራለሁ፡፡ አሁን ከተገነጠለችው ኤርትራ በቀር ሁሉንም ክፍላተ ሀገር አይቻለሁ፡፡ ስዞር ደግሞ ከተማ ብቻ አይደለም፡፡ እልም ያለ ገጠር ሁሉ የአምስት የስድስት ቀን መንገድ ተጉዤ እደርሳለሁ፡፡ ያኔ ቁጭ ብየ ከገበሬዎች ጋር አወራለሁ፡፡ ሳወራ ደግሞ ማስታዎሻዎች ባድም በሌላ እይዛለሁ፡፡ አሁን ይኸ ላንተ ብርቅ የመሠለህ ስነቃል ለነሱ ብዙም ቁም ነገሬ አይሉትም፡፡ ኑሯቸው ነው፡፡ እኔ ግን ከያንዳንዷ ብዙ እማራለሁ፡፡ ሌላው ያለኝ ጥሩ ነገር በወሬ መካል የሠማሁትን ተረትና ምሳሌ ሁሉ አልረሳም፡፡ ከሰማሁ ሰማሁ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ነኝ፡፡ ስለዚህ የማዳመጡ እድል አለኝ፡፡ እና የትም ቦታ ተማሪ ነኝ እኔ፡፡

የሓ፡- የእያንዳንዱ ወጎችህ መግቢያ ግን ተረት ነው፡፡ ‹‹እንግሊዞች እንዲህ ይላሉ›› ‹‹ህንዶች እንዲህ ይምናሉ›› ‹‹በአማራ እንዲህ ይባላል›› ‹‹በደቡብ እንዲያ አይነት ተረት አለ›› … ብለህ ትጀምራለህ፡፡ አትፈጥርም ግን?

ዲ/ን፡- እንዴት ብዬ! መች ተነካና ቀድሞ፡፡ እንዲያው አሜሪካኖች በዚህ በኩል ጎበዞች ናቸው፡፡ እያንዳንዷን የመሰብሰብ ልማድ አላቸው፡፡ እዚህም እኛ አገር ባለፈው ባህር ዳር የሄድኩ ጊዜ በዩኒቨርስቲው የአማርኛ ት/ት ክፍል ባደረገው ነገር ተገርሚያለሁ፡፡ በየወህኒ ቤቱ ዞረው፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ታራሚዎች ስነ ቃሎችን ሰብስበዋል፡፡ ትልቅ ነገር ነው፡፡

የሓ፡- ሁለገብነቱስ ከየት መጣ? በቋንቋም አለህ፡፡ በባህልም አለህ፡፡ በታሪክም አለህ፡፡ በብዙ ዘርፍ አይሃለሁ፡፡ ስለምትሳሳ ነው?

ዲ/ን፡- ኢህአዴግ በ83 ዓ.ም. ሲገባ ‹‹ብሶት የወለደው ጀግናው ሰራዊት›› ያለው አይነት ነገር ነው፡፡ ብሶት የወለደው ሲሆን እንደዚያ ነው የምትሆነው፡፡ የብቃት አይደለም፡፡ እና ደግሞ እኛ አገር ትንሽ ከፍ ብለህ ስትታይ ብዙ ይጠበቅብሃል፡፡ በተረታችን ‹‹አፍ ያግባው ከብት ያለው ስትባል አፍ ያለው አለች›› እንደተባለው አይነት ነው፡፡ ለዚያ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ተቆርቋሪነት አለኝ፣ እውቀቱን ግን የሚበልጡኝ አሉ፡፡ ቢያንስ ግን ከዝምታ መናገር ይሻላል፡፡

የሓ፡- እዚህ ላይ አልተሰራም እንስራበት የሚል ጥቆማም ነው ልበል?

ዲ/ን፡- ልክ ነው፡፡ ቁጭት አለኝ፡፡ እኛ አገር ባወቅህ ቁጥር ንዴት ነው የሚጨምርብህ፡፡ በተናደድህ ቁጥር ደግሞ እድል ስታገኝ ምናልባት ሌሎችም ተናደው ከኔ የተሻለ ቢጽፉ ብለህ ትጽፋለህ፡፡

፫) መሰናክሎች፣ ማለፊያ ጥንካሬዎች

የሓ፡- በጣም መሰናክል የሆነብህ ነገር ምንድን ነው? እንዴትስ አለፍካቸው?

ዲ/ን፡- ብዙ ፈተናዎች ብዙ መሰናክሎች ይገጥሙኛል፡፡ ለምሳሌ የኔ ስራ እንደምታውቀው ወጭ ጠያቂ ነው፡፡ በያገሩ ስዞር በተለይ ብዙ ሊገዙ የሚገባቸው የራሳችን ቅርሶች አያለሁ፡፡ ብራናዎችን በተለይ፡፡ እነሱን ገዝቶ እንኳን ለለመለስ አለመቻሌ ነው አንዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ መንገዶችን እጠቀማለሁ፡፡ አንደኛ እንደህንዶች በቃሌ እይዘዋለሁ፣ አንዳንዱን እንደምንም በውድ ዋጋ እገዛዋለሁ፡፡ ይኼ ራሱ ሌላ ቁጭት ነው፡፡ የራስን ንብረት በዉድ መግዛት ያንገበግባል መቼም፡፡

፬) ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን አጥተን እንዳናጣው ነገር

የሓ፡- ሰው ሟች ነው መቼም፡፡ ከመሞቴ ቀድሞ ማን ከኔ ምን ይሻማ ትላለህ?

ዲ/ን፡- ምንም፡፡ ብዙ ሊገኝባቸው የሚችሉ ብዙ አፍ የሌላቸው ሰዎች አሉ በኛ አገር፡፡ የአብነት መምህራኑን ጨምሮ፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፡፡ እኛ አገር እኮ ዘጠናና መቶ አመት የሞላው ሽማግሌ ሰው ታገኛለህ፡፡ አንድ ሰው ደግሞ መቶ አመት ሲኖር እንዲሁ አይኖርም፡፡ በጣም ብዙ ህይወት ውስጥ ያልፋል፡፡ በጣም ብዙ መንግስት አይቷል፡፡ የነዚህ ሰዎች ታሪክ መሠረት ነው፡፡ አሁን ይኸን ሁሉ ‹‹ልሞትልሽ ነው፣ ልሄድልሽ ነው›› ፊልም ደጋግሞ ከመስራት የነዚህን ሰዎች ታሪክ ብቻ እንደወረደ ብትተርከው አጀብ ነበር፡፡ የአብነቱን ትምህርትማ ንቀነዋል፡፡ አውሮፓዉያኑ እዚህ ድረስ መጥተው እኛኑ አጥንተው ፒኤዲ ይመረቃሉ፡፡ በየሙያው መስክ ብዙ መናገር የማይችሉ ግን ቀርበህ ብታናግራቸው ለተናጋሪ የሚሆን ታሪክ አላቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ የምንጠቅሰው አሜሪካ እንዲህ ያለ ጥናት፣ እንግሊዝ ውስጥ፣ እትት እያልን ነው፡፡ የእንግሊዙ ጥናት ግን ለጋምቤላ ወይ ለጎንደር ህዝብ አገጥምም፡፡ ስለዚህ ሽሚያው ከኔ ይልቅ ለነዚህ ሊቃውንት በሆነ፡፡ ከሽማግሌዎች በሆነ፡፡ … የሚገርምህ ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ በሚል ታሪክ እነ ቢቢሲ እልፍ ፊልም ሰርተዋል፡፡ አሁንም መጥተዋል፡፡ ለምን እኛ ዝም አልን? ከኔማ ምን ይገኛል? ስንት ሊቅ ሲያልፍ ዝም ያልነውን?

የሓ፡- ከቅዱስ ያሬድ በፊትም ሆነ በኋላ በተለየ ክህሎት እገሌ የምትለው ጠቢብ አለህ?

ዲ/ን፡- አንድ ብቻ ወይ ሁለት ብቻ ወይ አስር ብቻ መቶ ብቻ አይደሉም፡፡ ብዙ ናቸው፡፡ እንዲውም እዚህ አገር የነበሩ ሰዎች ሁሉ በየመልካቸው ጠቢባን ነበሩ፡፡ የጦር ጠቢባን ነበሯት፡፡ የሃይማኖት ጠቢባ ነበሯት፡፡ የባህል፣ የስነ ስዕል፣ የስነ ህንጻ፣ … በእነዚህ በእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ናት ኢትዮጵያ፡፡ ደግሞ ያላወቅናቸው አንዳንዴ በየማኅበረሰቡ ስሄድ የምሰማቸው ተሰምተው የማያልቁ ጅግኖችም ጠቢባንም ኖረዋል፡፡ ስለዐለም አፈጣጠር የሚሰጡት ይትባህል፣ የዘመን አቆጣጠራቸው የተለየ ነው፡፡ ተረቶቻችንን እያቸው፡፡ ጋምቤላ የሚተረት ተረት ጎጃም አለ፡፡ ጎንደርም ትግራይም ጉራጌም፣ ወሎም የትም መልኩን ቀይሮ ታገኘዋለህ፡፡ ለምሳሌ አንበሳ በነዚህ ቦታዎች የተወከለበትን አስተያይ፣ ጦጣ እነዚህ ቦታዎች ላይ የተወከለችበትን አስተያይ፣ ሴቶቹ እንዴት ነው የሚገለጡት፣ ወንዶችስ? ፈጣሪስ? ብልጥና ሞኝስ? እነዚህ ዝም ብለው አልተገኙም፡፡ ይህን ያደረጉት ሁሉ ጠቢባን ናቸው፡፡

የሓ፡- ቢሆንም ‹‹ከጣትም ጣት›› እንደሚባለው የተለየ ችሎታውን ያየህለት የለም?

ዲ/ን፡- የማስበልጠው ወይ የማሳንሰው ጥበበኛ የለኝም፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የራሱ ነገር አለው፡፡ ቅዱስ ያሬድም የራሱ ነገር አለው፡፡ ቀደም ስትል እነ ርቱዕ ኃይማኖት አሉ፡፡ ወደዚህ ስትመጣ እነ አባ ባህሬን ያየህ እንደሆነ፣ ጎጃም ዋሸራ ሊቃውንቱን ያየህ እንደሆነ … ሁሉም በየመለኪያቸው ትልቅ ናቸው፡፡

፭) መርሆች፣ የህይወት ፍልስፍናው

የሓ፡- ስንት አገሮችን አየህ ከኢትዮጵያ ውጭ?

ዲ/ን፡- በጣም ብዙ፡፡

የሓ፡- እንዲያው ኢትዮጵያን የሚያህል አገር አጥተህ ነው በዚያው ያልቀረህ? አንድም አገር አላስጎመጀህ? ኧረ በዚህች አገር አይንማ ኢትዮጵያ ለምኔ ያስባለችህ አገር የለችም?

ዲ/ን፡- በምን ሚዛን? አንደኛ እናትህን ከሌላው ጋር አታነጻጽርም፡፡ ማነጻጸሪህም ሰውን ከሰው ከምታነጻርበት ይጠልቃል፡፡ ያንተ እናት አጭር ልትሆን ትችላለች፣ ገንዘብ ላይኖራት ይችላል፣ ወይ ትቆጣህ ይሆናል፡፡ ይሄ ግን እናትነቷን አያስለውጥም፡፡ እኔ በግሌ በተለያየ ምክንያት ዜግነታቸውን ቀይረው ይኖራሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ለምን አደረጉ አልልም፡፡ እኔ ግን ላደርግ አልችልም፡፡

የሓ፡- ፊልም ወይ ቴአትር ትመለከታለህ?

ዲ/ን፡- አይ እምብዛም ነኝ፡፡

የሓ፡- ሙዚቃም አታዳምጥ? ስዕልም አታይም?

ዲ/ን፡- ስዕል ካልከኝ፤ የተለያዩ ኤግዚብሽኖችን የማየት እድል ነበረኝ፡፡ እንዲያውም በይበልጥ ስዕል በግሌም ተጋብዠም የማየት ልምዱ አለኝ፡፡ ሌሎች ያልከኝ ዘርፎች ላይ ግን እንዳልኩህ እምብዛም ነኝ፡፡ ጊዜውም የለኝ፡፡

የሓ፡- ግን እኮ ‹‹የሳይንቲስቱ ልጅ ጥያቄ›› በሚለው ያለፈ ወግህ ላይ ስለ ፊልምና ፊልም ሰሪዎች አንዲት አሽሙር ሰንዝረህ ነበር፡፡ … (የጓደኛዋ አባት ‹ፍቅር እዚህም እዚያም›፣ ‹ትሄጅብኛለሽ›፣ ‹ፍቅር በኪችን ውስጥ› የተሠኙ የፍቅር ፊልሞች ላይ የሠራ ‹ታዋቂ አርቲስት›…) እኔም ያንን ሳነብ የኢትዮጵያን ፊልም በጠና አይተህ ታዝበኸዋል ብዬ ነበር፡፡ ተሳስቻለሁ ማለት ነዋ?

ዲ/ን፡- በእርግጥ ያልከውን ጽፌያለሁ፡፡ እኔም ያልኩህ እምብዛም ነኝ ነው እንጂ ጨርሶ አላይም ማለቴ አይደለም፡፡ በተለይ በአውሮፕላን ስሄድ አንዳንዴ አያለሁ፡፡ ወይ የጽሑፉ መሠረታዊ ሃሳብ ላይ አስተያየት እንድሠጥ እታደላለሁ፡፡ ወይ የፊልም ምርቃት ላይ እጋበዛለሁ፡፡ ወይ ልጆቼ ኢቢኤስ ላይ ሲመለከቱ አብሬ አያለሁ፡፡ ቴአትርም ላይ እንዲሁ፡፡ ግን በጣም አልፎ አልፎ፡፡ ማን የሚባል የፊልም ወይ የቴአትር ወይ የሙዚቃ ባለሙያ በየትኛው ሙያ ላይ አለ ብትለኝ ግን በደንብ እሰከማልለየው ድረስ ሩቅ ነኝ፡፡ እውነት ለመናገር ግን አስቤ ዛሬ ወይ ነገ ልከታተል ብዬ ያየሁበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ እዩኝ እዩኝ ብሎ የመጋበዝ ኃላቸውም ያን ያህል ይመስለኛል፡፡

የሓ፡- ታዲያ የእውቀት ምንጭህ ምንድን ነው?

ዲ/ን፡- በዋናነት መጻሕፍትን በማንበብ ነው ያወቅሁትን ሁሉ ያወቅሁት፡፡ ከሰዎች ጋር ስወያይም ትምህርት አለ፡፡

የሓ፡- መጽሐፎችስ ችግሮቻችንን እየተጠቀሱና እየተነቀሱ ናቸው? እንዲያውም የትኛው ቃለ መጠይቅህ ላይ እንደሆነ እረሳሁት እንጂ ‹‹ያልበላንን የምናክክ›› እንዳንሆን ስጋትህን ስትናገር ሰምቸሀለሁ ልበል?

ዲ/ን፡- ይሆናል፡፡ ግን ምን አለ መሠለህ? ባሁኑ ጊዜ በተለይ ደራስያን ሁለት አይነት አካሄድ አላቸው፡፡ ነጻነት ስትልና ኃፊነት ስትል ሁለቱ ይለያያሉ፡፡ አንዳንዶች ‹‹እኔ የህብረተሰቡን ችግር የመግለጽ ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ጥብብ ብቻውን ሊቆም አይችልም፡፡ ስጋ ያስፈልገዋል፡፡ ስጋው ደግሞ ማኅበረሰቡ ነው፡፡ ስለሆነም የማኅበረሰቡ ጉዳይ ከሌለበት ለምን ሲል ያነበዋል?›› ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ህጉ የሚከለክለኝ ሰዎችን ከሠዎች እንዳላጋድልና የማኅበረሰቡን ሞራል እንዳላበላሽ ባቻ እንጂ የመሠለኝን እንዳልጽፍ ሌላ ከልካይ የለብኝም፡፡ ለምንድን ነው የምገደደው? ጥበብን ስለጥበብ ብቻ በስሜት ነው የምጽፈው›› የሚሉ አሉ፡፡ ስለሆነም ለፍርድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ልክ ናቸው አይደሉም ለማለት ደግሞ መጽሐፎቹን ሁሉ ሰብስቦ አይቶና አጥንቶ በዚያ ላይ መነሳት ይጠይቃል፡፡ ያሉንም ኢትዮጵያ ውስጥ መጻሕፍት ይወጣሉ? በጣም ጥቂት፡፡ ከነሱዉም አብዛኛዎቹ ግጥሞች ናቸው፡፡ እጥረቱም ስላለ ነቅሰዋል ጠቅሰዋል ለማለት እንኳን አልደረሱም ባይ ነኝ በበኩሌ፡፡

የሓ፡- ስለ የሓ ቤተ ጥበብ የምትለን ካለህ?

ዲ/ን፡- አዲስ ሃሳብ ነው፡፡ ያው ለፍሬ የማድረሱ ነገር ላይ ከበረታችሁ እንደዚ ሁሉንም የኪነ ጥበብ ዘርፎች አማክሎ እንደ አማራጭ መገናኛ ሆኖ መቅረቡ ተገቢም ነገር ነው፡፡ ጊዜውም ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላቀ ኹኔታ አስፍታችሁ እንድትቀጥሉበት ተስፋ አለኝ፡፡

የሓ፡- በመጨረሻም?

ዲ/ን፡- ባንቀል እላለሁ፡፡ ባንንቀዋለል፡፡ ዝም ብለን ከመወፈር፣ ዝም ብለን ከምንቀጥን ከባድ ነገሮችን ማሰብ ብንጀምር፡፡ አሁን ሰሞኑን የምሰማቸው ነገሮች አሉ፡፡ አውሮፕላን ለመስራት ስለሞከሩት ወጣቶች፡፡ እንዲህ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ይሄን አዉሮፕላን ሰርቼ ተሳፍሬ ወደ ላይ እንደወጣሁ ብፈጠፈጥስ? ልፈጥፈጣ!›› አይነት ድፍረት ያስፈልጋል፡፡ እንጂ በዚህ ጊዜ ጫት ቤት፣ በዚህ ጊዜ ፊልም ማየት ብቻ፣ ኳስ መደገፍ ብቻ፣ ሴት ማተካካት ብቻ፣ እንቅልፍ ብቻ የትም አያደርሰንም፡፡

የሓ፡- እናመሰግናለን፡፡

ዲ/ን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

የሓ፡-

ምንጮቻችን

ቀጥተኛ ቃለ ምልልስ፣ የሓ ቤተ ጥበብ



አስተያየት እዚህ ያስቀምጡልን

ስም [*]ትክክለኛ ሰዉ መሆንዎን ያረጋግጡልን [*]አስተያየት እዚሁ ያስቀምጡልን


እስካሁን (2) አስተያየቶች ተሰጥተዉበታል


 www.yehaarts.com     2017-12-26
Selam,Thank you!


 selamawit kifle     2017-12-22
adnakih negn tade .i will call you.

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

እኔ የትም ቦታ ተማሪ ነኝ፡፡

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Read in PDF 2015-07-14 በየሓ ቤተ ጥበብ


ከዚህ ቀደም አብረዉን ከተጨዋወቱ እንግዶች መካከል

ሄኖክ አየለ(አዘጋጅ) ከጀርባ መሆን መልካም ነው።
ሄኖክ አየለ(አዘጋጅ) Read in PDF

የሓ፡- ያዘጋጀሃቸው ፊልሞችን እኔ ስቆጥር ፲፩ ደረሱ። እስኪ ፊልሞችህን አስቆጥረኝ።

ሄኖክ፡- ቁጠር። የመጀመሪያው ‹መስዋዕት›፣ ኹለተኛው ‹የወንዶች ጉዳይ፩›፣ ከዚያ ‹አልቦ›፣ ከዚያ ተጨማሪ ያንብቡ



ፈቃዱ ተ/ማርያም ቴአትር ልክፍት ነዉ፤ አንዳንዴ እንዲያዉም ጅል ያደርጋል፡፡
ፈቃዱ ተ/ማርያም Read in PDF

የሓ፡- በዋናነት ተዋናይ ብቻ ነህ ጋሽ ፍቄ። ግን የልብን ስሜት አውጥቶ ለመንገር ተዋናይነት ብቻ በቂ ነው?

ፈቃዱ፡- ሲቻል ነዋ ታዲያ። ጽሑፍ ወይ ሌላ ሙያ ላይ የለሁበትም ያን ያህል። ብችልና ተጨማሪ ያንብቡ



ግሩም ኤርሚያስ የጥበብ ሰው ጥግ የለውም፣ ከማኅበረሰብ ወዲያ፡፡
ግሩም ኤርሚያስ Read in PDF

የሓ፡- ብዙ ወጣቶች ፊልም መተወን እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እነሱንና አንተን እንዲህ ወደ ትወና ያማለላችሁ ምኑ ደስ ቢል ነው?

ግሩም፡- ያልተኖረ ህይወት መኖር ስለሚያስችል ይመስለኛል፡፡ ተጨማሪ ያንብቡ


መልእክተ የሓ

በዚህኛዉ ዐምድ እንዲጋበዙላችሁ የምትፈልጓቸዉን ሰዎች እንድትጠቁሙን ወይም ደግሞ የራስዎትን የህይወት ተሞክሮ ለማካፈል ፈቃደኛ ከሆኑ በዚህ በኩል ቢያገኙን ደስታዉን አንችለዉም፡፡

መገኛችን

ለገሀር፣ አዲስ አበባ

19686

yehaarts@gmail.com

+251 912 944937

ጉርሻ - Bonus

“ከፊደል ሀ፣ ከከተማ የሓ የሚቀድም የለም” ተብሏል፡፡ የአጋዝያን ምድር፣ የግዕዝ ቋንቋም መነሻ፣ የልዕልናችንም መጀመሪያ ነበረች፡፡ በብዙ ጥበብ የተንበሽበሽች፡፡ አሁን እምብዛም ሞቋት የማታድረዋ የሓ፤ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሁነኛ ዋና ከተማ ነበረች።

(2015-2024) © yehaarts