፩) ትውልድ(ቀንና ቦታ)፣ ቤተሠብ፣ ትምህርት
የሓ፡- እንግዳችን እንድትሆን ያለምንም ደጅ ጥናት ስለፈቀድህ ክብረት ይስጥልኝ በቅድሚያ፡፡
ግሩም፡- አመሰግናለሁ፡፡
የሓ፡- ያው በትውውቅ እንጀምር፡፡ ስለ ቤተሰብህና ስለ ትውልድ ስፍራህ እናስቀድም?
ግሩም፡- ታዲያ ይህንንማ አንተው ታውቀው የለ?
የሓ፡- እኔው ልመልሰው እሺ፡፡ አዲስ አበባ(ተክለ ሃይማኖት አካባቢ) ተወልደህ፣ እዚሁ አዲስ አበባ ትኖራለህ፡፡ ከዚያ ስትኖር ስትኖር ለአቅመ አዳም ደረስህ፡፡ ከዚያም ሚስት አገባህና የሁለት ልጆች አባትም ሆንህ፡፡ አሁን ከእነሱ ጋር በደስታ ትኖራለህ፡፡ በዚህ እንለፈው፡፡
፪) ሙያ፣ አስተዋጽዖ፣ ተሰጥዖ
የሓ፡- ብዙ ወጣቶች ፊልም መተወን እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እነሱንና አንተን እንዲህ ወደ ትወና ያማለላችሁ ምኑ ደስ ቢል ነው?
ግሩም፡- ያልተኖረ ህይወት መኖር ስለሚያስችል ይመስለኛል፡፡ የኔን ልንገርህ፡፡ ግሩም እንደ ግሩም ብቻ ቢሆን አንድ ነበር፤ ግሩም እንደተዋናይ ሆኖ ግን ብዙ ነው፡፡ ተዋናይ ስለሆንኩ እንደቦክሰኛ ኖሪያለሁ፣ እንደ ዶክተር ሆኛለሁ፣ … ወዘተ፡፡ ገና ያልሆንኳቸውንም እኖራለሁ፡፡ ስለዚህ ይመስለኛል ደስ የሚለው፡፡
የሓ፡- እንጂ ተከትሎ ለሚገኘው ገንዘብና እውቅና አይደለም?
ግሩም፡- ለኔ አይደለም፡፡ ይኼ እንግዲህ ጥልቅ የሆነ ስሜቴ ነው ብየ ነው የማስበው፡፡ በተረፈ እንደየሰው ደግሞ ሊለያይ ይችላል፡፡ አንዳንዴ ገንዘብ ፍለጋ ወይ እውቀት ፍለጋ ብሎ ሊመጣ ይችላል፡፡ አላውቅም ስለሌሎች፡፡ የኔ የውስጥ ስሜቴ የሚነግረኝ ግን እንዲህ ነው፡፡ በሙያው ለመቆየት የቻልኩት የህይወትን ጥግ የመፈተሽ እድሉ ስላለበት ነው፡፡ ለዚህ ነው የማይሰለቸኝ፡፡
የሓ፡- ስንት ፊልም ሰራህ?
ግሩም፡- ወደ አስራ አራት ደረሡ መሠለኝ፡፡
የሓ፡- በስንቱ ተሸለምክ?
ግሩም፡- ላስቆጥርሃ፡፡ መጀመሪያ በአምስተኛው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ በይሉኝታና በትዝታህ ፊልሞች ላይ ተሸልሚያለሁ፡፡ ባንድ ፌስቲቫል ላይ በሁለት ፊልም ታጭቶ በሁለቱም የተሸለመ ሌላ ሰው መኖሩን እንጃ፡፡ ቀጥሎ በስምንተኛው ፊልም ፌስቲቫል ላይ ደግሞ በአራት መቶ ፍቅር ፊልም፣ ቀጥሎ ‹ጉማ የፊልም አዋርድ› ላይ በጭስ ተደብቄ ፊልም፣ ሌላ ደግሞ ‹የአድማጮች ምርጫ› ላይ አምና በጭስ ተደብቄ፣ ዘንድሮ በላምባ ፊልም ተሸልሚያለሁ፡፡ ቁጠርና ቁጥራቸውን አንተው ድረስበት፡፡
የሓ፡- ላምባ ስትል ሌላ ጥያቄ መጣልኝ፡፡ ከትወናው በተጨማሪ ጽሑፉ ላይም ስምህን አየሁት ልበል?
ግሩም፡- እውነትም ስሜ የላምባን ጽሑፍ ከጻፉት እንዳንዱ ተጠቅሷል፡፡ ያ የሆነው ግን ድርሰቱ ላይ ያን ያህል ሚና ኖሮኝ አይደለም፡፡ እንዲያው ክሬዲቱን ሰጡኝ እንጂ ከማማከርና እንዲህ ቢሆን ከማለት ያለፈ አልነበረም ድርሻዬ፡፡ አይገባኝም ነበር፡፡
የሓ፡- ያው መቼም አንተ መርጠህ ነው የምትሰራው ይመስለኛልና ለምን ሰራኸው ላምባን?
ግሩም፡- በብዙ ምክንያት፡፡ አንደኛ ታሪኩን ወድጀው ነው፡፡ ሲደመር ገጸ ባህሪውን ወድጀዋለሁ፡፡ ሲደመር ፊልሙ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ወድጀዋለሁ፡፡ ገና የፊልሙን ጽሑፍ አይቼ ኋላ በታዳሚ የሚፈጠረውን እውቂያ ወድጀው ነው የሰራሁት፡፡ እንዳሰብኩትም ነበር፡፡
የሓ፡- ስለዚህ አንተ የምትቀበለው ጥበብ ለጥበብ ደንታ(art for the sake of art) የሚለውን እንጂ ጥበብ ለቢዝነስ ደንታ(art for the sake of business) አይደለማ?
ግሩም፡- አይደለም አዎ፡፡ እኔ በእኔ እምነት ጥበብ ለጥበብ ደንታ ነው መዋል ያለባት ባይ ነኝ፡፡ ግን በኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ስታየው ሁለቱም ቢኖሩ ክፋት የለውም፡፡ እኔ ግን በባህሪዬ የምመርጣቸው ፊልሞች የሆነ ነገር ማለት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ፊልም በጣም ኃይለኛ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ስለማምን የምሰራቸው ፊልሞች ሁሉ መልእክት አዘል እንዲሆኑ እለፋለሁ፡፡
የሓ፡- ባልሰራሁበት ኖሮ ያልከው ፊልም አለ? ወይ እንዲህ በሰራሁት ኖሮ ያልከው?
ግሩም፡- አሉ፡፡ አንድ ሁለት ፊልሞች አሉ፡፡ ታሪካቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ ጥሩ አዘጋጅ ስላላገኙ የተበላሹ ፊልሞች አሉ፡፡ ስክሪፕቱን ሳነበውና ኋላ ውጤቱን ሳይ አልዳረስ ብሎኝ ምነው ባልሰራሁባቸው ኖሮ ያልኳቸው ፊልሞች አሉ፡፡ ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ፊልም የዳይሬክተር ነው፡፡ የኛ ብቻ አቅም ወይ ጥረት ብቻውን ያለ አዘጋጁ ጉብዝና አይሰምርም፡፡ ተዋናይ ምን እሳት የላሰ ቢሆን አዘጋጁ ካልበረታ አያምርም፡፡ ስማቸውን ጥቀስ እንዳትለኝ እንጂ፡፡ አያስፈልግም፡፡
የሓ፡- አንተስ የራስህን ጥናት ሠርተህ፣ ገጸ ባህሪውን በራስህ የምትፈልግ ከሆነ ከዳይሬክተሮች ጋር እንዴት ነው የምትግባቡ? ታስቸግራለህ?
ግሩም፡- አይ አላስቸግርም፡፡ እንዲያውም ብዙ አዘጋጆች እንደሚሉኝ አቀልላቸዋለሁ፡፡ የራሴን የቤት ስራ ጥንቅቅ አድርጌ ጨርሼ ስለምቀርብ አላስቸግርም ይመስለኛል፡፡ ደግሞ ከቀረጻ በፊትም ከዳይሬክተሮች ጋር በብዙ መልኩ አብረን ነን፡፡
የሓ፡- ታዛዥ ነሃ?
ግሩም፡- በትክክል!
የሓ፡- መጽሐፍ ማንበብ ላይ፣ ፊልሞችን አዘውትሮ የማየት ላይ፣ ስዕሎችን መመልከት ላይ እንዴት ነው ልምድህ? የእውቀት ምንጮች ላይ ምን ያህል ጊዜ አለህ?
ግሩም፡- አሁን ያልካቸው ሁሉ የኔ ‹ሆቢዎቼ› ናቸው፡፡ መዝናኛዎቼም ጭምር፡፡ ፊልም በጣም አያለሁ - ባላይ ነው የሚገርመኝ፡፡ መጽሐፍት ጋር ወዳጆች ነን፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ መጽሐፍ ማንበብ በጣም ነው የምወደው፡፡ ሳልመርጥ፡፡ ምክንያቱም የህይወት ምግብ ናቸውና አእምሮዬን መመገብ አለብኝ፡፡ ስዕልም በተለያዩ ‹ጋለሪዎች› እየተዘዋወርኩ አያለሁ፡፡ በጣም ነው የምወደው፡፡
የሓ፡- ህንደኬ ቴአትርን እንዳየኸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እዚያ ላይ ‹‹ጀግና የጀግናን ጀግንነት አይክድም›› ብለዋል ጸሐፌ ትዕዛዙ፡፡ እነማን ናቸው ጀግኖችህ?
ግሩም፡- የመጀመሪያው የልብ ህሙማን ማዕከልን ያቋቋሙት ዶ/ር በላይ አበጋዝ፡፡ ከዚያ ደግሞ የህዳሴውን ግድብ የሚመሩት ኢ/ር ስመኝ በቀለ፡፡ እኔ እንዲያውም ሁሌ እላለሁ፡፡ የእነዚህን ሰዎች ምስላቸውን በቲሸርታችን አትመን ብንመሰክር ደስ ይለኛል፡፡ ከዚያ በላይ፡፡ ምክንያቱም ለህዝብ ያበረከቱትን ስታይ ጀግኖች ናቸው በውነት፡፡ በየዘርፉ አሉ፡፡ ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ጀግኖች የምላቸው እነማንን መሰለህ? ማኅበረሰብን የሚያገለግሉትን ሁሉ ነው! በህክምናውም ሁሉ፣ በምህንድስናውም ሁሉ፣ በውትድርናውም ሁሉ፣ በመምህርነቱም ሁሉ፣ በስነ ጽሑፉም ሁሉ፣ በሁሉም ዘርፍ ያለምንም ልዩነት የሚያገለግል ሁሉ ጀግናየ ነው! አለቀ፡፡
፫) መሰናክሎች፣ ማለፊያ ጥንካሬዎች
የሓ፡- ልትወጣ ነበር አሉ ኢትዮጵያን ትተህ፡፡ እውነት ነው?
ግሩም፡- አዎ፡፡ ከዚህ ሙያ በፊት ማለት ነው፡፡ ለመውጣት የሞከርኩትም አንዴ ብቻ ነበር፤ እሱ አልተሳካም፡፡ ጂቡቲ ደርሼ ተመለስኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ወደ ውጭ የመውጣት ጥሜ ተቆርጧል፡፡ ህይወቱ ደስ አይልም ነበር፡፡ ብዙ ነበር ፈተናው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የጻልኝን ተመልሼ አገኘሁት፡፡
የሓ፡- ሌላስ የማትረሳው ምን ፈተና ገጥሞህ ነበር? እንዴትስ አለፍከው?
ግሩም፡- ለፈተና ፊት መስጠት አያስፈልግም፡፡ እንዲህ አጣሁ፣ እንዲህ ነጣሁ ብሎ ችግርን ማክበር አያስፈልግም፡፡ ምንም ችግር አልገጠመኝም፣ ሁሉም አልጋ ባልጋ ነበር ለማለት አይቻለኝም፡፡
፬) ግሩም ኤርሚያስን አጥተን እንዳናጣው ነገር
የሓ፡- አሁን እጅህ ከምን ግሩሜ?
ግሩም፡- አሁን ሰፊ ጊዜ ሰጥቼ እየሰራሁ ያለሁት በጎ አድራጎት ነው፡፡ በእርግጥ በጣም በጎ አድራጊ ነኝ ለማለት ባልደፍርም ግን አልቦዘንኩም፡፡ የኩላሊት ማኅበሩ አምባሳደር እንደመሆኔ መጠን ትልቅ ሩጫ ላይ ነኝ፡፡ ከማኅበሩ ጋር፡፡
የሓ፡- በዚህ እድሜህ አትቆይም መቼም፡፡ ወጣትነትህ ሳያልፍ ማን ከኔ ምን ይውሰድ ትላለህ?
ግሩም፡- ሁለት ነገር፡፡ አንደኛ ወጣትነቴ ሳያልፍ ላደርገው የምችለው በተሠጠኝ ልክ መስጠት ይገባኛል፡፡ የምር ሙያዬን አክብሬ ልሰራ፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ያለኝን ልምድ ማካፈል፡፡ እናም፤ ወደዚህ ሙያ ከገባሁበት ሁለት አመት በኋላ በተጠራሁበት ት/ቤት ሁሉ እየዞርኩ ያለኝን ልምድ ሁሉ ለማካፈል ሞክሪያለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- ‹ሁራ ኮሚየኒኬሽንስ›፣ ‹ክሬቲቭ የፊልም ት/ቤት›፣ ‹ቶም የፊልም ት/ቤት›፣ ‹ወጋገን የፊልም ት/ቤት›፣ ‹ማስተርስ የፊልም ት/ቤት› እና ሌሎችም ለሚያሰለጥኗቸው ተማሪዎች ቢያንስ ለሁለትና ሶስት ጊዜ ተገኝቻለሁ፡፡
የሓ፡- ባንተ እምነት፣ አንተ በምትታደማቸው የኪነ ጥበብ ወይ የስነ ጥበብ ውጤቶች ላይ፤ ታሪኮች ከዚህ ከዚያም እየተነሱ ነው? ከየክፍለ ሀገራት፣ ከየክፍለ ዘመናት ታሪኮች በሚገባ እየተጠቀሱ ነው?
ግሩም፡- እኔ እንጃ፡፡ በእርግጥ ወደዚህ ወደ አዲስ አበባ የማዘንበል ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ግን ደግሞ ወጣ እያሉ የሚነካኩ ስላሉ ለእነሱ እውቅና መስጠትም ያስፈልጋል፡፡ ያም ቢሆን ብዙ የቤ ስራ እንዳለንም ደግሞ ይሠማኛል፡፡ የጥበብ ሰው ጥግ የለውም ነው የሚባል፡፡ ጥጉ ሁልጊዜ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የጥበብ ሰው ከሆንክ ሁሉንም መንካት አለብህ፡፡ ግን በሂደት የሚመጣ ይሆናል የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡
የሓ፡- ውክልና ላይስ? የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ የተለያዩ እምነቶች፣ የተለያዩ የእድሜ እርከኖች፣ ሁለቱም ጾታዎች፣ ሁሉም ሙያዎች፣ የተለያዩ ባህሎች፣ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ …. እኩል እየተወከሉ ነው? ላንዱ የሚሰጠውን ክብር ባንጻሩ ላለው ይሠጣል? ወይስ እልም ጭልም ያለ ነገር ነው?
ግሩም፡- ይኼ ከባድ ጥናት የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን እኔን በሚሰማኝ እንዳልከው ነው፡፡ እኩል ውክልና አለ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ለምሳሌ እንኳን የእድሜውን ነገር ብናይ ልክ አይደለም፡፡ ሴቶች ሲሳሉ በብዛት እድሚያቸው ከሃያ እስከ ሃያ ሰባት አካባቢ ነው፡፡ እንዲያውም የወንዶች ይሻላል፡፡ እንጂ ህጻናትን ያማከለ፣ አረጋዉያንን ያማከለ፣ በተለይ ደግሞ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችን፣ ልዩ ልዩ ይትባህሎችን፣ ልዩ ልዩ ዘርፎችን የመዳሰሱ ነገር ላይ እጠራጠራለሁ፡፡ ይኼም የእኛው የቤት ስራ ነው፡፡
፭) መርሆች፣ የህይወት ፍልስፍናው
የሓ፡- የምትከተለው የትወና መንገድ “Method acting” መሠለኝ፡፡ እንዴት ያለ ነው እሱ?
ግሩም፡- ስለ Method acting ከመናገሬ በፊት ትንሽ ስላመጣጡ ልናገር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዐለም ያስተዋወቀው ሩስያዊው ዳይሬክተርና ተዋናይ(Constantin Stanislaviski) ነው፡፡ እና፤ በዚያው በእሱ ዘመንም ሆነ በኋላ የእሱን አካሄድ በጠና የተቃወሙ ሰዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የትወና መንገድህን ስትመርጥ እንደየሰው ጠባይና ምርጫ ይለያያል፡፡ ለኔ ግን ‹‹መምሰል ሳይሆን መሆን›› በሚለው ትርጓሜው ተስማምቼና ተስማምቶኝ እየሰራሁበት ያለ መንገድ ነው፡፡
የሓ፡- ከሀገራችን ሁኔታ ጋርስ እንዴት ታስማማዋለህ? በተለያዩ ምክንያቶች ማስመሰል እንጂ ማድረግ እንዳትችል የሚያግዱህ ነገሮች የሉም?
ግሩም፡- አሉ፡፡ ለነገሩ እኔም ስቀበል ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ አልተቀበልኩትም፡፡ እውቀት እስከሆነ ድረስ የመመርመርና ከራስ ጋር የሚገጥመውን ወደ ውስጤ የማስገባት ኃፊነቱ የኔ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼን ሰው ሰራው እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ስላልሆነ በተረዳሁት መጠንና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በሚፈቅደው ልክ እተገብረዋለሁ፡፡ ባህል አለ፡፡ ትውፊት አለ፡፡ ኃይማኖት አለ፡፡ ለነሱ ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ እሆናለሁ ብዬ የምተላለፈው የኢትዮጵያ ስርዐት አይኖርም፡፡
የሓ፡- ምን ያህልስ ችሎታን ለመግለጥ ሁነኛ መንገድ ነው? እንዳልከኝ አቢይ አንድምታው ‹‹መምሰል ሳይሆን መሆን ከሆነ›› ማንም ሰው ሊሰራው አይችልም? ለምሳሌ ሰካራም ሆኖ ለመስራት ጥንብዝ ብሎ መስከር፣ አይነ ስውር ሆኖ ለመስራት አይንን ማጥፋት፣ ወዘተ ከሆነ፤ ማንም ተራ ሰው ሊያደርገው አይችልም ወይ? አይቀልም?
ግሩም፡- አይቀልም፡፡ ባንተው ምሳሌ ሰካራም ሆኖ ለመስራት ጠጥቶ ብቻ የውጭ አወለጋገዱን ማምጣት ብቻ አይደለም ልኩ፡፡ ይጠልቃል፡፡ የስካርን የውስጥ ስሜት ጥግ ድረስ ማወቅ ነው ዋናው፡፡ እኔም ምሳሌ ልንገርህ፡፡ እዚህ ቁጭ ብለህ ስለ ሱዳን ግጥም ልትጽፍላት አትችልም፡፡ እንዲህ ነሽ እንዲያ ነሽ ለማለት ወደሷ መሄድ አለብህ፡፡ ሱዳን ሄደህ ተራራ ካላት ተራራዋን፣ ቁልቁለት ካላት ቁልቁለቷን ባይንህ በብረቱ ማየት አለብህ፡፡ ኖረህባት ማጥናት አለብህ፡፡ የህዝቦቿን የውስጥ ረሃብ፣ የውስጥ እንባ፣ የውስጥ ሰቀቀን ማወቅ አለብህ፡፡ ሱዳን ሄደህ፡፡ ከዚያ ግጥም ልጻፍ ብትል አንድም ታሳምናለህ፣ ደግሞም ልክ ነህ፡፡ አለበዚያ ግን ግምት ነው የሚሆንብህ፡፡ ግምትህን ደግሞ ማንም አያምንልህ፡፡ የኔም የትወና መንገድ እሱ ነው፡፡ ውስጥ ገብቼ ዋናውን ፍለጋ፡፡ የተሠጠኝን ገጸ ባህሪ ህመም፣ ደስታ፣ ዉጣ ውረድ እንዳለ ላውቅለት እፈልጋለሁ፡፡ ልጋራው እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያ እንደሱ እንደራሱ ሆኜ እነግርለታለሁ፡፡
የሓ፡- ለትወና ብለህ ገብተህበት በዚያው የለመደብህ ባህሪ አለ?
ግሩም፡- የለም፡፡ ዋናው የተዋናይ ብቃት መለኪያውም እሱ ነው፡፡ ባልኩህ መንገድ የተሰኝን ገጸ ባህሪ እሆናለሁ፣ ስጨርስ ግን ወደ ራሴ እመለሳለሁ፡፡ የተዋጣለት ተዋናይ ማለትም ሙሉ በሙሉ ስሜት ውስጥ መግባት፣ ስራው እስኪያልቅ በስሜት መቆየት፣ ስራው ካለቀ በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከስሜት መውጣት የሚችል ነው፡፡
የሓ፡- ፖለቲካ ላይ እንዴት ነው ተሳትፎህ? በዞረበትም አልዞር ባይ ነህ እንዴ?
ግሩም፡- ፖለቲከኞችን አልሰማህም ማለት ነው፡፡ በእነሱ አይን እኮ ሁሉም ነገር ፖለቲካ ነው፡፡ ስትበላም ሆነ ስትተነፍስ ሁሉም ከፖለቲካ ክበብ እንደማይወጣ ነው የሚተነትኑት፡፡ ስለዚህ በዞረበት አልዞርም ልልህ አልችልም፡፡ ከዚያ ይልቅ በጣም የማደንቃቸው ፖለቲከኞች አሉ፡፡ ከደጋፊም ከተቃዋሚም ማለቴ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የጥበብ ሰው ፍርድ ሰጭ ሊሆን አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ይኼ ነው ልክ ያኛው ነው ከማለት ይልቅ እውነቱን እንዳለ መግለጥ ብቻ ነው የጥበብ ሰው ኃፊነት፡፡ እነእገሌ እንዲህ ያምናሉ፣ እነገሌ ደግሞ እንዲያ፡፡ የሁሉም ነሃ፡፡
የሓ፡- በመጨረሻም
ግሩም፡- አመሰግናለሁ፡፡ ጥሩ ነው የቆየነው፡፡
የሓ፡- ደንበኛ እንሆናለን፡፡
ግሩም፡- ያለ ጥርጥር፡፡
ምንጮቻችን
ቀጥተኛ ቃለ ምልልስ፣ የሓ ቤተ ጥበብ
አስተያየት እዚህ ያስቀምጡልን
እስካሁን (5) አስተያየቶች ተሰጥተዉበታል
ብሩክ 2015-08-04
ሠናይ ቆይታ ነበር እናመሰግናለን፡፡በተረፈ ግሩሜ ለምትሠራው ሁሉ እግዚአብሔር ይርዳህ፡፡ለጀማሪ የፊልም ባለሞያዎች በየቦታው እየሄድክ ልምድህን እንደምታካፍል ሁሉ ለእኛም ለተመልካቾች ;ለአንባቢዎች እና ለአድናቂዎችህ ከሙያዊ አስተያየት ; ገጠመኝዎች ባለፈ የህይወት ተሞክሮዎችህን በተለያዩ መንገዶች እንደምታስተላልፍ ተስፋ እናደርጋለን በርታ፡፡ ለ ግሩሜ
ስም ያልጠቀሰ 2015-08-03
Great!And, I feel sorry for Lamba film(since I heard as it has been stolen)
ታመነ ዋሌ 2015-08-03
ቋቅ ግሩሜ! አሳማኙ ተዋናይ። መርጦ ሠሪው። ሙያውን አክባሪ።
ዳኘ 2015-08-01
ብዙ ቁምነገሮች አሉበት። ጠያቂው ወደ ጥሩ ነገር መርቶታል ግሩምም በሚገባ ተከትሎታል።
Habtamu Mihirete 2015-08-01
የሓዎች እሥካሁን ባልነበረ፣ መንጣሪ አጥቶ ተዘግቶ በኖረ መንገድ አዲስ የጥሩ ነገር መዳረሻ የሚሆን ቀዳዳ ከፍታችኋል። ደስ ይላል። ደግሞም በርቱ።