የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ፷ኛውን ዐመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ በዐሉን ማክበር ጀመረ፡፡
ዉብርስት በልስቲ
2015-07-10
ለአዲሱ ዘመናዊ የቴአትር ቤት ግንባታ የተጣለውን የመሰረት ድንጋይ ተከትሎ ፷ኛውን ዐመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ እንደሚያከብር የገለጸው አንጋፋው ቴአትር ቤት - ብሔራዊ፡፡ ዋናው በዐል ህዳር ፫፣ ፳፻፰ዓ.ም. እንደሚሆን በተለያዩ ‹ፖስተሮች› የተገለጸ ቢሆንም ቅደመ ዝግጅቶች ግን ከወዲሁ ተጀምረዋል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚኖሩት ነጻ የሙዚቃ ድግሶች በተጨማሪ ልዩ ልዩ ጥበባዊ ክንዉኖችም እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ በቅድመ በዐሉም ሆነ ከበዐሉ በኋላ የመጀመሪያዎቹ የቴአትር ቤቱ ከያንያንና መስራቾች በብዙ እንደሚታሰቡ የሚጠበቅ ሲሆን ቴአትር ቤቱና የቴአትር ታዳሚዎች በቅርበት የሚወያዩበት መድረክ እንደሚፈጥርም ይታሰባል፡፡
ዜናውን ለማጠናቀር በቴአትር ቤቱ አካባቢ በተዘዋወርንበት ጊዜ ያነጋገርናቸው የቴአትር ተመልካቾችም ‹‹ቴአትር ቤቱ እዚህ እንዲደርስ የደከሙ ቀዳሚዎች በዘጋቢ ፊልም፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር እና በሌሎች መንገድ ሊነገርላቸው ይገባል፡፡ በዐሉም ይልቁን የሚደንቀው በዚሁ መልክ ነውና ከወዲሁ እንዲታሰብበት›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡