ገ ረ ገ ራ     በማንኛዉም የመጽሐፍ አዟሪና መደብር ይገኛል።     Order4Delivery (እዚሁ ያዝዙ)
ዐውደ ዜና

ሰሞነኛ ወሬዎች፣ አዳዲስ ነገሮች፣ የመርሐ ግብር ጥቆማዎች

በዓሉ ግርማ - ቤርሙዳ ቴአትር

በዓሉ ግርማ - ቤርሙዳ ቴአትር

 ታደለ አያሌዉ       2024-02-19

በዓሉ ግርማ

ቤርሙዳ

፨፨፨፨፨፨፨

ደራሲ፡ ዉድነህ ክፍሌ

አዘጋጅ፡ ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር)

አቅራቢ፡ ሀገር ፍቅር ቴአትር (ዘወትር እሁድ፣ በ8፡30)

በብዙዎች የተደነቀዉን ቴአትር፣ በእቅዴ መሠረት ትናንትና ተመለከትሁት። በእርግጥ ‹በእቅዴ መሠረት› ያልሁት ለይምሰል ነዉ እንጂ፣ እስከዛሬ ያላየሁበት ትክክለኛ ምክንያት ግን፣ ቅናት ስለመሆኑ እኮ ጥርጥር የለዉም። እንዴት ይኼ ሁሉ ተመልካች ኖረዉ? እንዴት በዚህ ደረጃ ተወደደ? ያስቀናል!

የሆነዉ ሆኖ፣ ቅናቴ አልፎልኝ፣ ‹በዓሉ ግርማ - ቤርሙዳ› የተባለዉን ቴአትር ተመለከትሁት። በአጭሩ፣ ግሩም ሥራ ነዉ። ሌላ ሌላዉ ቀርቶ፣ የመብራት እና የድምጽ አጠቃቀሙ ብቻ ይበቃል። እንኳንስ ታሪኩ የበዓሉ ግርማ ሆኖ፣ እንኳንስ ደራሲዉ ዉድነህ ክፍሌ ሆኖ፣ እንኳንስ አዘጋጁ ዶ/ር ተሻለ ሆኖ፣ እንኳንስ ትወናዉ በዚያ ደረጃ ሆኖ፣ የመድረክ ዲዛይኑ ብቻ ይበቃል።

እዉነት ለመናገር፣ በአንድ ወቅት ከጋሽ ጌትነት እንየዉ ቃለ መጠይቅ የሰማሁት እንደሚመስለኝም፣ ታሪካዊ ሰዉን በቴአትር ማምጣት ፈተናዉ ዋዛ አይደለም። ለምሳሌ፣ ምናልባትም አብዛኞቻችን የቴአትሩ ተመልካቸች፣ በዓሉ ግርማን ከነአነጋጋሪ ታሪኩ እና ሥራዎቹ እናዉቀዋለን። ምክንያቱም የራሱን መጽሐፎች አንብበናል፣ ስለ እሱ የተጻፉትን እና የተነገሩትን ሁሉ ሰምተናል። ስለዚህ፣ እንደማይታወቅ የምናብ ፍጡር፣ በዓሉን ‹ከአሁን አሁን ምን ይገጥመዉ ይሆን› ብለን የምንጓጓበት ታሪክ ቴአትሩ ሊያመጣልን አይችልም። ታሪኩን ከቴአትሩ በፊት አዉቀነዋላ!

ቃል በቃል ባይሆንም፣ ጋሽ ጌትነት እንየዉ ስለ ‹የቴዎድሮስ ራእይ› ያለዉ እንደዚሁ ነዉ። “ቴዎድሮስ ከቋራ መነሳቱ፣ የተዋበች ባል መሆኑ፣ ጠላቶቹን ድባቅ መትቶ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለመሆን መብቃቱን፣ ከእንግሊዞች ጋር መዋጋቱን፣ በመጨረሻም መቅደላ ላይ በጀግንነት ራሱን መሰዋቱን የማያዉቅ ሰዉ አይኖርም። መቼስ የቴዎድሮስ መጨረሻ በመቅደላ መሆኑን የሚያዉቅ ተመልካች፣ ‹መጨረሻዉ ምን ይሆን› ብሎ ሊጓጓ አይችልም።

እንግዲያዉስ ጋሽ ጸጋዬ ገ/መድኅን ከብርሃኑ ዘርይሁን በኋላ፣ ጌትነት እንየዉ ደግሞ ከጋሽ ጸጋዬ በኋላ ለምን ቴዎድሮስን በቴአትር አመጡልን? እኛ ተመልካቾቹስ ያን ያህል ወደን እና ደጋግመን ያየነዉ ለምንድነዉ? እኔ በበኩሌ የጋሽ ጌትነት እንየዉን ቴዎድሮስ ቢያንስ ዐምስት ጊዜ አይቸዋለሁ።

ተወዳጁ ‹በዓሉ ግርማ› ቴአትርም እንደዚሁ አዘጋጁንም ሆነ ደራሲዉን እንደፈተናቸዉ ጥርጥር የለዉም።ሆኖም ግን፣ ያንን የምናዉቀዉን ታሪክ፣ ልክ እንደ አዲስ በስስት እንድናየዉ ማድረግ ችለዋል። ምክንያታዊ እና ዉብ ቃለ ተዉኔት፣ ምክንያታዊ እና የሚጋባ የመድረክ ስሜት፣ አሳማኝ አተዋወን እና ሌሎችም ነገሮች ስክትክት ብለዉበታል። ዉድ ቴአትር መሆኑን እና በቁርጠኝነት የተሠራ መሆኑን፣ ሦስት ደቂቃ ለማትሞላዉ እና በትዝታ የመንግሥቱን ቢሮ ያየንባት ትእይንት ብቻ በቂ ማስረጃ ናት። ያለፈ ታሪክን (ትዝታን)፣ አሁናዊ ድርጊቶችን እና የወደፊቱን ለማሳየት የሄደበት ጥበብ ድንቅ ነዉ።

(ይቀጥላል)

ታደለ አያሌዉ

yehaarts.com

3 ከ 33

ሊያጋሩን የሚፈልጉት መረጃ (የዜና ጥቆማ) ካለዎ ያግኙን

መገኛችን

ለገሀር፣ አዲስ አበባ

19686

yehaarts@gmail.com

+251 912 944937

ጉርሻ - Bonus

“ከፊደል ሀ፣ ከከተማ የሓ የሚቀድም የለም” ተብሏል፡፡ የአጋዝያን ምድር፣ የግዕዝ ቋንቋም መነሻ፣ የልዕልናችንም መጀመሪያ ነበረች፡፡ በብዙ ጥበብ የተንበሽበሽች፡፡ አሁን እምብዛም ሞቋት የማታድረዋ የሓ፤ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሁነኛ ዋና ከተማ ነበረች።

(2015-2024) © yehaarts